በሕይወት መንገድ ላይ ያሉ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች
በማታውቀው መንገድ ላይ እየተጓዝክ ሳለህ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች ተተክለው ብታገኝ እንደ እንቅፋት አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? በጭራሽ! ከዚያ ይልቅ መንገድ ጠፍቶህ እንዳትባዝን የሚረዱህ ጠቃሚ ነገሮች እንደሆኑ አድርገህ እንደምትመለከታቸው የታወቀ ነው።
ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ ስለ መጓዝስ ምን ለማለት ይቻላል? አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች ሳይኖሩ በተሳካ ሁኔታ መጓዝ ይቻላልን? በጥንት ጊዜ የነበረ አንድ የአምላክ ነቢይ በዚህ ረገድ የሰው ልጅ ያለው ችሎታ ውስን መሆኑን ገልጿል። “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ሲል ተናግሯል።—ኤርምያስ 10:23
ታዲያ ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዴት ማግኘት ይቻላል? ትክክለኛውን አቅጣጫ ሊጠቁም የሚችለው የሰው ልጆች ፈጣሪ ሲሆን ምሳሌያዊዎቹ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶችም የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት እንዲህ ይላል:- “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።”—ኢሳይያስ 30:21
አዎን፣ የአምላክ ቃል ለማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ የሚሆን አስተማማኝ መመሪያ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 48:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የሚያሳዝነው ግን አብዛኛው የሰው ዘር የሚጓዘው ከመለኮታዊ መመሪያ ውጭ በሆነ የሕይወት ጎዳና ላይ ነው። (ማቴዎስ 7:13) ያም ሆኖ ግን አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶቹ በማይነቃነቅ ሁኔታ ተተክለው ይገኛሉ! ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ በምትጓዝበት ጊዜ እነዚህን ምልክቶች በጥንቃቄ ትከተላለህን?