“እኛ ካቶሊኮች ከእነሱ ብዙ የምንማረው አለ”
በኢጣሊያ ባሪ የምትገኝ አንዲት አስተማሪ በሃይማኖት ታሪክ ክፍለ ጊዜ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ስታስተምር የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ከላይ ያለውን ተናግራለች። አስተማሪዋ የቪዲዮ ክሮችን ለማስተማሪያነት እንደምትጠቀም ለተማሪዎቿ ነግራቸው ነበር። ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው የ18 ዓመቱ ሮቤርቶ ይህን ሲሰማ የእሱም ሃይማኖት በውይይቱ ውስጥ እንዲካተት ሐሳብ አቀረበ። የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የሚባለውን የቪዲዮ ክር ለአስተማሪዋ ሰጣት። ሮቤርቶ ያመጣውን የቪዲዮ ክር ከመቀበሏም በላይ ክፍሉ ውስጥ ያሉት 30 የሚሆኑ ተማሪዎች በሙሉ ፊልሙን ተመለከቱ። “በአንድነታቸው፣ በድርጅቱ እንዲሁም በይሖዋ ምሥክሮች መካከል በሚታየው ጥልቅ ፍቅር ሁሉም ተደንቀዋል” ሲል ሮቤርቶ ገልጿል። “ከዚህ ይበልጥ ያስደነቃቸው በእያንዳንዱ ወር 40 ሚልዮን የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችና 36 ሚልዮን የንቁ! ቅጂዎች እንደሚታተሙ ማወቃቸው ነው።”
ቪዲዮውን ከተመለከቱ በኋላ በርካታ የሚሆኑ የሮቤርቶ የክፍል ጓደኞች “ይህን ያህል የተደራጃችሁ አይመስለኝም ነበር” የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል። አስተማሪዋ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ለክፍሉ ተማሪዎች እንዲህ ብላለች:- “እምነታቸው ምን ያህል እንዲተባበሩና እንዲደራጁ እንዳስቻላቸው ተመልከቱ። እኛ ካቶሊኮች ከእነሱ ብዙ የምንማረው አለ።” የቪዲዮ ፊልሙና ቀጥሎ የተደረገው የክፍል ውይይት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሻል ያለ ግንዛቤ ለማስያዝ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።