“በደመናት ውስጥ ጥበብን ያኖረ ማን ነው”?
“ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፣ ወዲያው:- ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፣ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ:- ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፣ ይሆንማል።” ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ የጻፋቸው እነዚህ የኢየሱስ ቃላት በጥንትዋ ፍልስጤም ይደረጉ ለነበሩት የአየር ሁኔታ ትንበያዎች በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። (ሉቃስ 12:54, 55) በአንዳንድ ሁኔታዎች በጥንት ጊዜ የነበሩ ሰዎች ምልክቶችን አይተው ትክክለኛ የአጭር ጊዜ ትንበያዎች ማድረግ ችለው ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ሜቲዮሮሎጂስቶች ምድርን የሚዞሩ ሳተላይቶችን፣ የሞገድ ፍጥነት መለኪያ ራዳር እንዲሁም ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ኮምፒዩተሮችን የመሳሰሉ የረቀቁ መሣሪያዎች ተጠቅመው በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚኖረውን የአየር ጠባይ ይተነብያሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ትንበያቸው ትክክል አይሆንም። ለምን?
የአየር ጠባይን በትክክል ለመተንበይ አዳጋች የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ስላሉ ነው። ለምሳሌ ያህል በሙቀትና በዕርጥበት መጠን፣ በአየር ግፊት እንዲሁም በነፋስ ፍጥነትና አቅጣጫ ላይ የሚከሰቱ ያልተጠበቁ ለውጦች ጉዳዩን ሊያወሳስቡ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሳይንቲስቶች ሙሉ በሙሉ ያልተረዷቸው በፀሐይ፣ በደመና እና በውቅያኖሶች መካከል ውስብስብ የአሠራር ትስስሮች አሉ። ከዚህም የተነሳ የአየር ጠባይ ትንበያ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ ያልሆነ ሳይንስ ነው።
የሰው ልጅ ስለ አየር ሁኔታ ያለው የተገደበ እውቀት ቀጥሎ ለኢዮብ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ያስታውሰናል:- “የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? . . . የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? . . . በደመናት ውስጥ ጥበብን ያኖረ ማን ነው? ወይስ ለሰማይ ክስተቶች ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? [NW] የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቆጥር የሚችል ማን ነው? . . . የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?”—ኢዮብ 38:28–37
የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ ይሖዋ አምላክ ነው እንጂ ሰው አይደለም የሚል ነው። አዎን፣ ሰዎች ምንም ያህል ጥበበኞች መስለው ቢታዩም እንኳ የፈጣሪያችን ጥበብ እጅግ በጣም የላቀ ነው። መንገዳችንን የተቃና ማድረግ እንድንችል የሱን ጥበብ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ አስፍሮ መስጠቱ ከልብ አፍቃሪ መሆኑን ያሳያል።—ምሳሌ 5:1, 2