ከእናት ፍቅር የሚበልጥ
በምድር ውስጥ ባሉ ባቡር ጣቢያዎች፣ በሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ወይም ግርግር በሚበዛባቸው ጎዳናዎች ላይ እናቶች የወለዷቸውን አራስ ልጆች ይጥላሉ። አንዳንድ ጊዜ የማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ቆሻሻ ሲሰበስቡ እናታቸውን ፍለጋ አልቅሰው አልቅሰው የደከሙ አራስ ልጆች ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ ሳይቀር ተጥለው ያገኛሉ። ኦ ኤስታዶ ደ ሳው ፓውሎ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ “በጎዳናዎች ላይ የሚጣሉ አራስ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።” እርግጥ ነው እናትየው ያደረገችው ነገር ከጊዜ በኋላ ይጸጽታት ይሆናል። ምንም እንኳ በዚህ ድርጊቷ ልጅዋ ሊሞት እንደሚችል ብታውቅም ጥላው ትሄዳለች።
‘አንዲት እናት ምን ሊገጥመው እንደሚችል ሳታውቅ እንዴት ልጅን ያክል ነገር ሜዳ ላይ ጥላ ትሄዳለች?’ ብለህ ትገረም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓይነቱን አሳዛኝ ሁኔታ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ፈጣሪ ለሕዝቦቹ ያለውን ስሜት ለማነጻጸር ተጠቅሞበታል። “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፣ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም።”—ኢሳይያስ 49:15
በእርግጥም ከየትኛዋም ሰብዓዊ እናት በበለጠ አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር ጥልቅ ከመሆኑም በላይ ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ያስባል። ወጣትም ሆንክ አዋቂ ማንኛውም ዓይነት ችግር ቢገጥምህ የተጣልክ ያክል ሆኖ አይሰማህ። ፈጣሪህ አንተን ለመርዳት ይፈልጋል፤ ስለ ደኅንነትህም ያስባል። መዝሙራዊው “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ዘወትር ይጠነቀቅልኛል” ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 27:10፣ የ1980 ትርጉም
በዓለም ዙሪያ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች የሚሰራጩት ‘ብቻውን እውነተኛ አምላክ’ ስለሆነው ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ለመስጠት ነው። ይህን እውቀት በአድናቆት የሚቀበሉ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችላሉ።—ዮሐንስ 17:3