‘እንደ ሊባኖስ ዝግባ ወደ ላይ ያድጋል’
ውብ በሆኑት የሊባኖስ ተራራዎች ላይ አርዝ አራብ (ትርጉሙ “የጌታ ዝግባዎች” ማለት ነው) በመባል የሚታወቁ ዛፎች ይገኛሉ። በአንድ ወቅት ተራራዎቹን በሙሉ ይሸፍኑ የነበሩት ምንጊዜም ልምላሜ የማይለያቸው ግርማ ሞገስ የተላበሱ እነዚህ ዛፎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከማንኛውም ሌላ ዛፍ ይበልጥ ማለትም 70 ጊዜ ያህል ተጠቅሰዋል።
ቅዱሳን ጽሑፎች የሊባኖስ ዝግባዎች ያላቸውን ግርማ ለመግለጽ “መልካም” እና “የከበረ” የሚሉትን ቃላት ይጠቀማሉ። (መኃልየ መኃልይ 5:15፤ ሕዝቅኤል 17:23) የዝግባ ዛፍ ግዙፍነቱና የእንጨቱ ጥንካሬ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ለቤትና ለመርከብ እንዲሁም ለቤት ውስጥ ዕቃዎች መሥሪያ ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል። የእንጨቱ መዓዛና ደመቅ ያለው ቅላቱ በጣም ማራኪ ሲያደርገው በውስጡ ያለው ከፍተኛ የሙጫ መጠን ደግሞ እንጨቱ እንዳይበሰብስ እንዲሁም በተባይ እንዳይጠቃ ለመከላከል አስችሎታል። የዝግባ ዛፎች እስከ 37 ሜትር የሚደርስ ቁመትና ወደ 12 ሜትር የሚጠጋ የጎን ስፋት በመያዝ በጣም አስገራሚ የሆነ ቁመትና ግዝፈት እንዲሁም ጥልቅ የሆኑ ጠንካራ ሥሮች አሏቸው። አንዳንድ ዘመናዊ የደን ባለሙያዎች የዝግባ ዛፎችን “የዕፅዋቱ ዓለም የክብር ዘውድ” ብለው መሰየማቸው ምንም አያስደንቅም!
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሕዝቅኤል መሲሑን ትንቢታዊ በሆነ መንገድ አምላክ ራሱ ከሚተክለው የዝግባ ዛፍ ቀንበጥ ጋር አመሳስሎታል። (ሕዝቅኤል 17:22) እንዲያውም “ዝግባ” ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ጽኑ መሆን” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። ዛሬ በተመሳሳይ የመሲሑ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ረጅም እንደሆነውና ጫናዎችን መቋቋም እንደሚችለው የዝግባ ዛፍ ሁሉ ‘በእምነት ጸንተው መቆምና መጠንከር’ ያስፈልጋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:13) ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ተጽዕኖዎችን በጽናት በመቋቋም እንዲሁም ንጹሕ አቋምንና ለአምላክ የማደርን አኗኗር በጽናት በመከተል ነው። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ደጋግ ሰዎች . . . እንደ ሊባኖስ ዝግባ ወደ ላይ ያድጋሉ” ተብለው ተገልጸዋል።—መዝሙር 92:12 የ1980 ትርጉም