“አምላክ የሚፈልገው እንደ እናንተ ያሉትን ነው”
ክርስቲያኖች ‘ስለ ጌታ ብለው’ ከዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ጋር ሲተባበሩ ‘በጎ ማድረጋቸው ነውና ምስጋና’ እንደሚያተርፍላቸው ሊጠብቁ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 2:13–15) በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ከጥቂት ጊዜ በፊት በአንድ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ የአውራጃ ስብሰባ ባደረጉ ጊዜ የገጠማቸው ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነበር።
በስብሰባው የመጀመሪያ ዕለት የኮሌጁ የጥበቃ ፖሊሶች ከዚህ ቀደም ሌሎች ባደረጓቸው ስብሰባዎች እንደገጠማቸው በዚህም ዕለት ብዙ ቁጡና ለመተባበር ፈቃደኛ የማይሆኑ ተሳታፊዎች ይገጥሙናል ብለው ስላሰቡ ራሳቸውን በደንብ አዘጋጅተው ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ያልነበራቸው እነዚህ ሰዎች አስደሳች ነገር ሊመለከቱ ነው!
የጥበቃ ፖሊሶቹ እንደ ወትሮው በመግቢያ በሮች ላይ ቆመው ወደ ግቢው የሚገባውንና ከዚያ የሚወጣውን እያንዳንዱን መኪና መፈተሻቸውን ተያያዙት። ፍተሻው ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም የስብሰባው ተሳታፊዎች የሚሰጧቸው ወዳጃዊ ሰላምታ፣ የሚያሳዩአቸው ትዕግሥትና አክብሮት አስገረማቸው። እንደ ሌላው ጊዜ እምቢተኝነት፣ ክርክርና ስድብ አልገጠማቸውም። አንድ የፀጥታ ጥበቃ መኮንን “ከሌሎች እንግዶች በተለየ መልኩ ትሕትናችሁና ክብራችሁን የምትጠብቁ ሰዎች መሆናችሁ ለሁላችንም ግልጽ ነበር” ሲል ተናግሯል።
የጥበቃ ፖሊሶቹ አዛዥ የይሖዋ ምሥክሮች ተባባሪ ሰዎች መሆናቸውን ካስተዋለ በኋላ “የታረመ ድንቅ ጠባይ ያላችሁ ናችሁ” መኪናዎቹን መፈተሽ አያስፈልግም ሲል ወሰነ። በመሆኑም “JW” የሚል ምልክት የተሰጣቸው መኪኖች ያለ ምንም ፍተሻ እንዲገቡ ተደረገ።
ስብሰባው እንዳበቃ የጥበቃ ፖሊሶቹ አዛዥ ምሥክሮቹን በቅርቡ በሌላ አጋጣሚ እንገናኛለን ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። “እንዲህ ዓይነት የታረመ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አይተን አናውቅም” ካሉ በኋላ “አምላክ የሚፈልገው እንደ እናንተ ያሉትን ነው” ብለዋል። እንዲህ ያለው ምስጋና ሰዎች ‘የዓይን ምሥክር የሆኑለትን መልካሙን ሥራቸውን አይተው አምላክን ያከብሩ’ ዘንድ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘መልካም አኗኗራቸውን ጠብቀው እንዲመላለሱ’ ተጨማሪ ማበረታቻ ይሆንላቸዋል።—1 ጴጥሮስ 2:12