የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
እውነተኛውን አምላክ ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ ዋጋ አስገኘ
በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት በሐሰት አምልኮ ተበክሎ ነበር። ሆኖም የጣዖት አምልኮ በተንሰራፋበት በዚህ ሁኔታ ሥር ልቡን በቀጥታ ወደ አምላክ ያዘነበለ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው ኢዮሣፍጥ ይባላል። ነቢዩ ኢዩ እሱን በተመለከተ “እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” ሲል ተናግሯል። (2 ዜና መዋዕል 19:3) በተመሳሳይም ዛሬ በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለመፈለግ ‘ልባቸውን አዘጋጅተዋል።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) በምዕራብ አፍሪካ ካለችው ከቶጎ የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ ይህን ያረጋግጣል።
ካዚሚር ትምህርቱን የተከታተለው በካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የቆረበው የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ይሁን እንጂ ካዚሚር 14 ዓመት ሲሞላው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆመ። ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ባለማስቀደሱ ወደ እሳታማ ሲኦል እጣላለሁ፤ ይህ እንኳ ባይሆን መንጽሔ መግባቴ የማይቀር ነው የሚል ስጋት አድሮበት ነበር።
ካዚሚር ትምህርት ቤቱ ውስጥ በሳምንት አንድ ጊዜ አንድ ላይ ተሰብስበው መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያጠኑ ወጣቶች ጋር ገጠመ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በግሉ ማንበብ ጀመረ። ካዚሚር አንድ ወቅት ላይ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኘው ከባሕር የወጣ አስፈሪ አውሬ አነበበ። (ራእይ 13:1, 2) ይህን ጉዳይ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኑን መሪ ሲጠይቀው አውሬው በእውን ያለ መሆኑንና ቃል በቃል ከባሕር እንደሚወጣም ነገረው። ካዚሚር የሚኖረው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ብዙም ሳይርቅ በመሆኑ ማብራሪያው እረፍት ነሳው። ከአውሬው የመጀመሪያ ሰለባዎች መካከል አንዱ እሱ እንደሚሆን በእርግጠኛነት አመነ።
ካዚሚር ከአውሬው ርቆ በስተ ሰሜን ወደሚገኘው በረሃማ ቦታ ለመሸሽ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ። ዕቅዱን ለአንድ የክፍል ጓደኛው ነገረው። የክፍል ጓደኛው የይሖዋ ምሥክር ስለሆነ ቃል በቃል ከባሕር የሚወጣ ይህን የመሰለ አውሬ አለመኖሩን አረጋገጠለት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ካዚሚር በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ተጋበዘ። በስብሰባዎቹ የተደሰተ ከመሆኑም በላይ አዘውትሮ ይገኝ ጀመር። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለትም ተስማማ።
ካዚሚር በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ ከቤተሰብ ተቃውሞ ተነሳበት። ቤተሰቦቹ የቀድሞ አያቶችን በማምለክ የሚካፈሉ ከመሆናቸውም በላይ ከመሥዋዕት የተረፈ ደሙ ያልፈሰሰ ሥጋም ይበሉ ነበር። ካዚሚር ሥጋውን ለመብላት ፈቃደኛ አለመሆኑን በትሕትና ሲገልጽ ዝተው ቤቱን ለቅቆ እንዲወጣ ጠየቁት። ካዚሚር ዛቻውን ሳይፈራ ተቀመጠ፤ ቤተሰቦቹም እንደዛቱበት አላደረጉበትም። ሆኖም ለሦስት ወራት ያህል በቤቱ ውስጥ ይቀርብ የነበረው ምግብ ይህ ዓይነት ሥጋ ብቻ ነበር። ካዚሚር በቂ ምግብ የማግኘት ችግር ቢገጥመውም እንኳ ይህንንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን በጽናት አሳልፏል።
ካዚሚር መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን በመቀጠል ራሱን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ በቅቷል። ከጊዜ በኋላ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ተሾመና ቶጎ ውስጥ በተካሄደው የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አራተኛውን ክፍል ተካፈለ። አሁን በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ፈቃደኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
አዎን፣ ንጉሥ ዳዊት “[ይሖዋን] ብትፈልገው ታገኘዋለህ” ሲል የተናገራቸው ቃላት በብዙ ሁኔታዎች ሥር ምንኛ እውነት ሆነው ተገኝተዋል።—1 ዜና መዋዕል 28:9
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ካዚሚር (በስተቀኝ) በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በፈቃደኝነት ያገለግላል