‘ልጅህን አሠልጥነው’
በግብርና ሥራ ውጤታማ መሆን የሚቻለው እንዲሁ ሜዳ ላይ ዘር በትኖ በመሄድና ከጥቂት ወራት በኋላ ለአጨዳ በመመለስ አይደለም። ማሳውን ማለስለስን፣ ዘር መዝራትን እንዲሁም ውኃ ማጠጣትንና አድጎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ እንክብካቤ ማድረግን የሚጨምር አድካሚ ሥራ የሚጠይቅ ነው።
ይህ ሂደት ምሳሌ 22:6 እውነት መሆኑን በሚገባ ሊያሳይ ይችላል፤ ጥቅሱ “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው [“አሠልጥነው፣” NW]፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ይላል። በእርግጥም ልጅን በተሳካ ሁኔታ ለማሳደግ ወላጅ የሚሰጠው ሥልጠና ወሳኝ ነው።
ሆኖም ዛሬ ባለው ልቅ ዓለም ውስጥ ብዙ ወላጆች ይህን ምክር አይከተሉም። ወላጆች፣ ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው መወጣት መማር አለባቸው በሚለው ፈሊጥ ሲመሩ ልጆቻቸውን እርግፍ አድርገው ይተዋቸዋል። ይህ ዓይነቱ እርምጃ ወጣቶችን በሥነ ምግባር ያልተገሩና ያልታረሙ ሰዎች ለሚያሳድሩት መጥፎ ተጽእኖ ያጋልጣቸዋል።—ምሳሌ 13:20
ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከትንንሽነታቸው ጀምረው አምላካዊ ሥልጠና በመስጠት በውስጣቸው ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ቢቀርጹባቸው ምንኛ የተሻለ ይሆናል! ከስንት ዓመት ጀምሮ? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከሕፃንነት ጀምሮ’ ሲል ይናገራል። ወጣቱ ጢሞቴዎስ ይህ ዓይነት ሥልጠና አግኝቶ ነበር። እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ፣ ጢሞቴዎስ ‘እንዲማርና’ ‘እንዲረዳ’ ብለው “ቅዱሳን መጻሕፍትን” ደጋግመው በማስተማር በአእምሮው ላይ ቀርጸውበት ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? ይህ ዓይነቱ ሥልጠና “መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” እንዲያገኝ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15
በተመሳሳይ ዛሬ ወላጆች ‘መልካም ሥራን ለመሥራት’ ‘የማይታክቱ’ ከሆነ የተትረፈረፉ በረከቶችን ያጭዳሉ። (ገላትያ 6:9) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል” ሲል ተናግሯል።—ምሳሌ 23:24