የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“በጊዜውም አለጊዜውም” መስበክ
ጦርነት ቦስኒያን እና ሄርዜጎቪናን ባናወጠበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍተኛ ሰቆቃ ደርሶባቸዋል። በዚያ ፈታኝ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ለነዋሪዎቹ ማጽናኛና ተስፋ ለመስጠት የተቻላቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል። ቀጥሎ የቀረበው ጽሑፍ ለተወሰነ ጊዜ በሳራዬቮ ያገለገለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከጻፈው ደብዳቤ ላይ የተወሰደ ነው።
“እዚህ ኑሮው ከባድ ቢሆንም ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። የአገሬው ተወላጅ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት ጽናት እጅግ የሚደነቅ ነው። ምንም ቁሳዊ ነገር ባይኖራቸውም እንኳ በጣም ግሩም የሆነ መንፈስ አላቸው። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወጣቶች ባጠቃላይ ማለት ይቻላል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ናቸው። አዳዲስ አስፋፊዎች በዚህ ዓይነቱ ቅንዓት ይበረታታሉ። በመሆኑም አገልግሎት ከጀመሩበት ከመጀመሪያ ወር አንስቶ በወር 60 ወይም ከዚያ በላይ ሰዓት በአገልግሎት ማሳለፋቸው አዲስ ነገር አይደለም።
“ከቤት ወደ ቤት ከመስበክ በተጨማሪ ሰዎችን ማግኘት የምንችልባቸውን ሌሎች የተለያዩ ዘዴዎች ሞክረናል። ለምሳሌ ያህል ከተማው ውስጥ በሚገኙ በርካታ የቀብር ቦታዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማበርከት ጥሩ ውጤት አግኝተናል።
“በሆስፒታሎች ውስጥም ምሥክርነቱ እየተሰጠ ነው። በሳራዬቮ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በልብ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚሠራ ዋናው ሐኪም ‘የልብ በሽታን መከላከል የሚቻልበት መንገድ’ የሚል የሽፋን ርዕስ የያዘውን የታኅሣሥ 8, 1996 ንቁ! ወሰደ። መጽሔቶቹን ሌሎች ዶክተሮችም ማግኘት እንዲችሉ ተጨማሪ ቅጂዎች እንዲመጣለት ጠየቀ። ከዚያም ምሥክሮቹ እርሱ ሕክምናቸውን የሚከታተልላቸውን ታካሚዎች በሙሉ እንዲያነጋግሩ ተፈቀደላቸው። በመሆኑም በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከ100 መጽሔቶች በላይ ከአልጋ ወደ አልጋ ተበርክቷል። አብዛኞቹ ታካሚዎች አንድ ሰው ማጽናኛና ተስፋ ለመስጠት ሆስፒታል መጥቶ ሲያነጋግራቸው ይህ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
“በሌላ ጊዜ ደግሞ ወንድሞች ወደ ሕፃናት ሕክምና መስጫ በመሄድ ለሕፃናት የሚስማሙ ርዕሶች የያዙ መጽሔቶችን አበረከቱ። ከዚህ በተጨማሪ ዋናዋ ሐኪም ለንባብ ክፍሉ የሚሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ጥቂት ቅጂዎች ወሰደች። አሁን ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ እናቶች በየቀኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ለልጆቻቸው ያነብቡላቸዋል። እንዲሁም ዶክተሯን ቤቷ ሄዶ ለማነጋገር ዝግጅት ተደርጓል።
“በሳራዬቮ ውስጥ የተለያየ አገር ዜጎች የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የኔቶ [የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ማኅበር] ወታደሮች ይገኛሉ። እነዚህም ሳይቀር የተጣራ ምሥክርነት ደርሷቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ጉድ ኒውስ ፎር ኦል ኔሽንስ ከተባለው ቡክሌት ጋር በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በመጠቀም ከታንክ ወደ ታንክ እየሄድን እንሰብካለን። የኢጣሊያ ወታደሮች በሚኖሩበት ሰፈር ከ200 መጽሔቶች በላይ አበርክተናል። የሚያስገርመው ብዙ የኢጣሊያ ወታደሮች ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተነጋግረው እንደማያውቁ ቢናገሩም በሳራዬቮ ከእኛ ጋር የመነጋገር አጋጣሚ አግኝተዋል።
“አንድ ቀን አንድ ታንክ ከመንገድ ወጣ ብሎ ቆሞ ነበር። ታንኩን በያዝኩት ጃንጥላ ሳንኳኳ አንድ ወታደር ብቅ አለ። ሽፋኑ ላይ ‘የሰላም መልእክተኞች—እነማን ናቸው?’ የሚል ርዕስ ያለውን መጠበቂያ ግንብ አሳየሁት። ወታደሩ አየት አደረገኝና ‘መቼስ የይሖዋ ምሥክር ነኝ እንዳትለኝ፤ ነህ እንዴ?’ ሲል ጠየቀኝ። የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ሲያውቅ ‘በጣም የሚያስገርም ነው፤ ደግሞ እዚህም አላችሁ! ለመሆኑ በዚህች ምድር ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የማይገኙበት ቦታ ይኖራል?’ ሲል ተናገረ።”
ሐዋርያው ጳውሎስ “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” የሚል ምክር ሰጥቷል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) በዓለም ዙሪያ እንደሚገኙ የእምነት አጋሮቻቸው ሁሉ በሳራዬቮ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ከአልጋ ወደ አልጋና ከአንዱ ታንክ ወደሌላው እየሄዱም ጭምር ይህን በመፈጸም ላይ ናቸው!