ባለ ሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮችን አመሰገኑ
ከማድሪድ በስተ ደቡብ ምዕራብ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የስፔይኗ የወደብ ከተማ የካዲዝ ከንቲባ የሆኑት ዶና ቲዮፌል ማርቴኔስ ለይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሜዳልያ (ፎቶው ከላይ ይታያል) ሸለሙ። ሜዳልያው እንዲህ የሚል ጽሑፍ አለው:- “የይሖዋ ምሥክሮች ለከተማው ጥቅም በማሰብ ላደረጉት ትብብርና ላከናወኑት ሥራ ከካዲዝ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተሰጠ የአድናቆት መግለጫ።” የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ሽልማት የተሰጣቸው ምን ሠርተው ነው?
ምሥክሮቹ የከተማውን ስታዲዮም የተወሰነ ክፍል በማደስ ላከናወኑት ሥራ የተሰማቸውን አድናቆት ለመግለጽ የተሰጠ ሽልማት ነበር። በርካታ በሆኑ የሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በካራንዛ ስታዲዮም የእግር ኳስ ሜዳ ታችኛው ወለል ላይ ያሉትን የመጸዳጃ ክፍሎች በአዲስ መልክ ለመሥራት በፈቃደኝነት እርዳታ አበርክተዋል። በአሁኑ ጊዜ በስታዲዮሙ የሚገለገሉ ሰዎች ሁሉ ከተገጠሙት የቧንቧ መስመሮች፣ የመጸዳጃ ቤት ዕቃዎችና የወለል ንጣፎች ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
ላለፉት ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ከካዴዝ ከተማ መስተዳድር ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርተው ቆይተዋል። በየዓመቱ የከተማው መስተዳድር የይሖዋ ምሥክሮች በዓመት አንዴ ለሚያደርጉት የአውራጃ ስብሰባ በካራንዛ ስታዲዮም እንዲጠቀሙ በደግነት ሲፈቅድላቸው ቆይቷል። ስለዚህ ምሥክሮቹ ስታዲዮሙ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ለማድረግ ደስተኞች ናቸው።
ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች አልፎ አልፎ ከሚያከናውኑት የጉልበት ሥራ በተጨማሪ ሕዝቡን በሌላ መንገድ ለመርዳትም የከተማውን ነዋሪዎች ዘወትር ይጎበኛሉ። የአምላክን መንግሥት “ምሥራች” ያውጃሉ። እርግጥ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አገልግሎት የሚካፈሉት ከሰዎች ምስጋና ለማግኘት ብለው አይደለም። አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት ኢየሱስ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ እንዲሰብኩና ‘ከአሕዛብ ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ የሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19) እንዲህ በማድረግ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ‘የጽድቅ መንገድ’ በማስተማር ኅብረተሰቡን የመጥቀም ምኞት አላቸው።—ምሳሌ 12:28