ታስታውሳለህን?
በቅርብ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? ከሆነ፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ትችል እንደሆነ ተመልከት:-
◻ ጳውሎስ “ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች [“አምባሳደሮች፣” የ1980 ትርጉም] ነን” ሲል የተጠቀመበት መግለጫ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? (2 ቆሮንቶስ 5:20)
በጥንት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ አምባሳደሮች ይላኩ የነበረው ግጭት በሚፈጠርባቸው ወቅቶች ሲሆን በግጭቱ ምክንያት ጦርነት እንዳይነሳ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ይደራደሩ ነበር። (ሉቃስ 14:31, 32) ኃጢአተኛው የሰው ዘር ዓለም ከአምላክ የራቀ በመሆኑ አምላክ ያቀረበውን የማስታረቂያ ሐሳብ ለሰዎች እያስታወቁ ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲመሠርቱ ለማሳሰብ የተቀቡ አምባሳደሮቹን ልኳል።—12/15 ገጽ 18
◻ የአብርሃምን እምነት ያጠናከሩለት አራት ነገሮች ምንድን ናቸው?
አንደኛ፣ አምላክ የተናገረውን በመከተል በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት አሳይቷል (ዕብራውያን 11:8)፤ ሁለተኛ፣ እምነቱ ከተስፋው ጋር በጣም የተቆራኘ ነበር (ሮሜ 4:18)፤ ሦስተኛ፣ አብርሃም አዘውትሮ ከአምላክ ጋር ይነጋገር ነበር፤ እንዲሁም አራተኛ፣ አብርሃም የአምላክን መመሪያ በተከተለ ጊዜ ይሖዋ ድጋፍ ሰጥቶታል። ዛሬ እነዚሁ ነገሮች እምነታችንን ሊያጠናክሩልን ይችላሉ።—1/1 ገጽ 17, 18
◻ “ወደ ፈተናም አታግባን” የሚለው አባባል ምን ትርጉም ይዟል? (ማቴዎስ 6:13)
የእርሱን ትእዛዝ እንድንጥስ በምንፈተንበት ጊዜ አምላክ እንድንወድቅ እንዳይፈቅድ መለመናችን ነው። ይሖዋ ተሸንፈን ‘ለክፉው’ ለሰይጣን እጃችንን እንዳንሰጥ ሊመራን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 10:13)—1/15 ገጽ 14
◻ አንድ ሰው ለሠራው ኃጢአት የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?
ለአምላክ ከመናዘዝ በተጨማሪ መጸጸትና “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” ማፍራት ያስፈልጋል። (ሉቃስ 3:8) የንስሐ መንፈስና የሠራነውን ስህተት ለማስተካከል ያለን ፍላጎት የክርስቲያን ሽማግሌዎችን መንፈሳዊ እርዳታ እንድንሻ ይገፋፋናል። (ያዕቆብ 5:13-15)—1/15 ገጽ 19
◻ ትሑት ለመሆን መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
ትሑት ሰው ትዕግሥተኛና ቻይ ነው፤ እንዲሁም ከመጠን በላይ ስለ ራሱ አያስብም። ትሕትና እውነተኛ ወዳጆችን እንድታፈራ ያስችልሃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን በረከት ያስገኝልሃል። (ምሳሌ 22:4)—2/1 ገጽ 7
◻ በኢየሱስ ሞትና በአዳም ሞት መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት ምንድን ነው?
አዳም በፈጣሪው ላይ ያመፀው ሆን ብሎ ስለሆነ መሞቱ የሚገባው ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ‘ምንም ኃጢአት ስላላደረገ’ በፍጹም ሞት አይገባውም ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:22) ስለዚህ ኢየሱስ ሲሞት ኃጢአተኛው አዳም በሞተበት ጊዜ ያልነበረው ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ማለትም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ይዞ የመቀጠል መብት ነበረው። ይህም በመሆኑ የኢየሱስ ሞት የሰው ልጆችን በመቤዥት ረገድ መሥዋዕታዊ ዋጋ አለው።—2/15 ገጽ 15, 16
◻ በሕዝቅኤል ትንቢታዊ ራእይ ላይ የታየው ከተማ ምን ያመለክታል?
ከተማው ቅዱስ ባልሆነ ሥፍራ መካከል የሚገኝ ስለሆነ ምድራዊ ነገር መሆን አለበት። ስለዚህ ከተማው ጻድቅ የሆነውን ምድራዊ ኅብረተሰብ የሚጠቅም ምድራዊ አስተዳደር የሚያመለክት ይመስላል።—3/1 ገጽ 18
◻ ኢየሱስ በ33 እዘአ የማለፍ በዓልን ሲያከብሩ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበው ለምንድን ነበር?
ኢየሱስ እግር የማጠብ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መደንገጉ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያቱ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወንድሞቻቸውን ለማገልገል የትሕትናና የፈቃደኝነት መንፈስ እንዲያዳብሩ እየረዳቸው ነበር።—3/1 ገጽ 30
◻ ሌሎችን በምናስተምርበት ጊዜ ከተፈጥሮ ችሎታችን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?
ተማሪዎቹ ሊኮርጁ የሚችሉት ያዳበርናቸውን ባሕርያትና መንፈሳዊ ልማዶቻችን ናቸው። (ሉቃስ 6:40፤ 2 ጴጥሮስ 3:11)—3/15 ገጽ 11, 12
◻ የሕዝብ ተናጋሪዎች ጥቅስ የማንበብ ችሎታቸውን ማሻሻል የሚችሉት እንዴት ነው?
በመለማመድ ነው። አዎን፣ ምንም ሳይደነቃቀፉ ማንበብ እስኪችሉ ድረስ ከፍ ባለ ድምፅ ደጋግሞ በማንበብ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ በቴፕ ክር የሚገኝ ከሆነ አንባቢው የሚያጠብቅበትንና ድምፁን የሚለዋውጥበትን ቦታዎች ማዳመጡ እንዲሁም የስሞችና ያልተለመዱ ቃላት አጠራር እንዴት እንደሆነ ልብ ማለቱ ጥበብ ነው።—3/15 ገጽ 20
◻ አንድ ሰው ሲሞት ‘መንፈሱ ወደ አምላክ የሚመለሰው’ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? (መክብብ 12:7 NW)
መንፈሱ የሕይወት ኃይል ስለሆነ ‘ወደ እውነተኛው አምላክ ይመለሳል’ ሊባል የሚችለው ግለሰቡ ወደፊት በሕይወት ለመኖር ያለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ በአምላክ እጅ መሆኑን ነው። አንድ ሰው ወደ ሕይወት እንዲመለስ ለማድረግ መንፈሱን ወይም የሕይወት ኃይሉን መልሶ መስጠት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (መዝሙር 104:30)—4/1 ገጽ 17