ግፍ—ለዘላለም የሚያከትምበት ጊዜ ቀርቧል!
“ዓመፅ አንድን ብሔር ለአደጋ ይዳርጋል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“በቤት ውስጥ የሚፈጸም ግፍ።”—ኡ ግሎቡ፣ ብራዚል
“በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ግፍ።”—ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል፣ ካናዳ
በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ የወጡት እነዚህ ርዕሰ ዜናዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ አስደንጋጭ አዝማሚያ መኖሩን ይጠቁማሉ። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ እንደገለጸው “ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ዓመፅ በሁሉም ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ መጥቷል።”
አንዳንድ አሳሳቢ የሆኑ አኃዛዊ መረጃዎችን ተመልከት:-
ግድያ። በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን በየዕለቱ 1,250 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላሉ። ከዚህ የተነሳ “በአህጉሩ ካሉት አገሮች ግማሽ በሚሆኑት ከ15-24 በሚደርስ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ሞት በሁለተኛ ደረጃ መንስዔ ተደርጎ የሚጠቀሰው ግድያ ነው።”
በልጆች ላይ የሚፈጸም ግፍ። በልጆች ላይ የሚፈጸም አካላዊ፣ ጾታዊና ስሜታዊ በደል በዓለም ዙሪያ የሚገኝ ችግር ነው። ለምሳሌ ያህል “በኢንዱስትሪ በበለጸጉ በርካታ አገሮች ውስጥ በጎልማሶች ላይ የተካሄዱ ጥናቶች ከ10%-15% የሚሆኑ ልጆች የጾታ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ልጃገረዶች ናቸው።”
በሴቶች ላይ የሚፈጸም ግፍ። በ1997 ባለሙያዎች በዓለም ዙሪያ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ላይ ያካሄዱትን ጥናት ሲያጠናቅቁ “በዓለም ላይ በእያንዳንዱ አገር ማለት ይቻላል በሴቶች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት መንስዔ ከሆኑት ዓበይት ነገሮች አንዱ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ግፍ” እንደሆነ ደምድመዋል። (ሂውማን ራይትስ ዎች ዎርልድ ሪፖርት 1998) በቤት ውስጥ የሚፈጸም ግፍ በጣም የተስፋፋ ቢሆንም የዚያኑ ያህል ታፍኖ ዝም የሚባል ችግር በመሆኑ “አቤቱታ የማያሰማው የ20ኛው መቶ ዘመን አሳሳቢ ጉዳይ” ተብሏል።—ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል፣ ካናዳ
በተመሳሳይ መንገድ በኖኅ ዘመን ምድር ‘በግፍ ተሞልታ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:9-12) ሆኖም ይሖዋ አምላክ ‘ለቀደመው ዓለም ሳይራራ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋት ውኃን ሲያወርድ’ ያን ‘የጽድቅ ሰባኪ’ እና ቤተሰቡን አድኗቸዋል። በዘመናችንም አምላክ ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል። አምላክ ዓመፀኛና ክፉ የሆኑትን ሰዎች አስወግዶ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ይህችን ምድር ወደ ገነትነት ሲለውጣት ‘እግዚአብሔርን በመምሰል የሚመላለሱ ሰዎችን’ በሕይወት ይጠብቃቸዋል። (2 ጴጥሮስ 2:4-9፤ 3:11-13) በቅርቡ ግፍ ለዘላለም እንደሚያከትም ማወቅህ አያስደስትህም?