በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ለምን አስፈለገ?
“ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙ ሰዎች እንኳ እርሱ አስተዋይና ታላቅ አስተማሪ እንደነበር ያምናሉ። በእርግጥም እርሱ እስከዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው ነው።” (ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ) ለመሆኑ “እርሱ” ማን ነው? የክርስትና እምነት መስራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ምንም እንኳ ኢንሳይክለፒዲያው ከላይ የተጠቀሰውን ቢልም ኢየሱስ ክርስቶስ በምሥራቃውያንም ሆነ በሌሎች አገሮች ለሚኖሩ በመቶ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍታቸው ላይ የተጠቀሰ ምናልባትም ስሙ ብቻ ትዝ የሚላቸው እምብዛም የማያውቁት ሰው ነው። አልፎ ተርፎም በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት ምሁራንና ቀሳውስት ኢየሱስን በትክክል እንደማናውቀው በመናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ስለ እርሱ ሕይወት በሚያወሱ አራት ዘገባዎች (ወንጌሎች) ሐቀኝነት ላይ ጥርጣሬ ይዘራሉ።
የኢየሱስ የሕይወት ታሪክ የወንጌል ጸሐፊዎች ፈጥረው የጻፉት ሊሆን ይችላልን? በጭራሽ! እውቁ የታሪክ ምሁር ዊል ዱራንት አራቱን የወንጌል ዘገባዎች ከመረመሩ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአንድ ትውልድ ውስጥ የኖሩ ጥቂት ተራ ሰዎች ይህን የመሰለ ከፍተኛ የመለወጥ ኃይልና ተወዳጅነት ያለው ሰው፣ ይህን የመሰለ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃና ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለመፈልሰፍ ከቻሉ በወንጌሎች ውስጥ ከተጻፉት ተአምራት ሁሉ ይበልጥ ለማመን የሚያዳግት ተአምር ይሆናል። ከሁለት ምዕተ ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት በኋላ የክርስቶስን ሕይወት፣ ባሕርይና ትምህርት ጨምቆ የሚያቀርበው ታሪክ አሁንም ቢሆን በአመዛኙ ግልጽና በምዕራቡ ዓለም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆነውን ገጽታ ይዟል።”
ሆኖም የእርሱ ተከታዮች ነን የሚሉ ሰዎች በፈጸሙት ተግባር የተነሳ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትኩረት ሊሰጡት እንደማይገባ በማሰብ ገሸሽ የሚያደርጉት ሰዎች አሉ። በጃፓን የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ‘የእርሱ ተከታዮች ናጋሳኪ ላይ የአቶሚክ ቦምብ ጥለዋል። ናጋሳኪ ደግሞ በጃፓን ከሚገኙ ከአብዛኞቹ ከተሞች ይበልጥ ብዙ ክርስቲያኖች ይገኙባት ነበር’ ይላሉ። ሆኖም አንድ ታካሚ ዶክተሩ የሰጠውን መመሪያ ሳይከተል ቢቀርና ከበሽታው ባይድን ሐኪሙን ተወቃሽ ማድረግ ትችላለህን? ክርስቲያን ነን ብለው የሚናገሩ አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ የሰጠውን የሰው ልጆችን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል መመሪያ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ችላ ብለውታል። ሆኖም ኢየሱስ ለዕለት ተዕለት ችግሮቻችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሰው ልጆች ለሚደርሱባቸው መከራዎች የሚጠቅም መፍትሄ ሰጥቷል። ከዚህ የተነሳ የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብና ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር እንድታውቅ እንጋብዝሃለን።