‘ወደፊት የሚገጥመንን አርቆ ለማየት’ የሚያስችል ጥበብ
“እነርሱ የማመዛዘን ችሎታቸውን ያጡና ማስተዋል የሌላቸው ሕዝብ ናቸው። ጥበበኛ ቢሆኑ ኖሮ ይህን ያስተውሉና ወደፊት የሚገጥማቸውን አርቀው ይመለከቱ ነበር።”—ዘዳግም 32:28, 29 ቤክ
እነዚህ ቃላት እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ቆመው ሳሉ ሙሴ ለእነርሱ የተናገራቸው ናቸው። ሙሴ እስራኤላውያን ይሖዋን ችላ ስለሚሉበትና ድርጊታቸው ስለሚያስከትልባቸው መዘዝ የማያስቡበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት እየተናገረ ነበር። ከዚያ በመቀጠል በነበሩት መቶ ዘመናት በርካታ ነገሥታትን ጨምሮ የእስራኤል ሕዝብ የአምላክን ማስጠንቀቂያዎች ችላ ብሏል።
ለምሳሌ ያህል ሰሎሞን ከይሖዋ አምላክ በስተቀር ሌሎች አማልክት የሚያመልኩ ሰዎችን እንዳያገቡ የሚከለክለውን መለኮታዊ ትእዛዝ ያውቅ ነበር። (ዘዳግም 7:1-4) የሆነ ሆኖ ሰሎሞን “ብዙ እንግዶች ሴቶች” አገባ። ውጤቱ ምን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም።” (1 ነገሥት 11:1, 4) ምንም እንኳ ሰሎሞን ጠቢብ ቢሆንም የአምላክን መመሪያ ሳይታዘዝ ቢቀር ‘ወደፊት የሚገጥመውን ነገር አርቆ ለመመልከት’ የሚያስችል የማመዛዘን ችሎታ ይጎድለው ነበር።
እኛስ እንዴት ነን? በሕይወት ዘመናችን የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች በበቂ ሁኔታ አስቀድመን ካሰብንባቸው ብዙ ችግሮች ማስወገድ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች ‘ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳቸውን እንዲያነጹ’ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር ነው። ሆኖም ብዙዎች ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ችላ ቢሉ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል አርቆ ለማየት የሚያስችል የማመዛዘን ችሎታ የላቸውም። ለምሳሌ ያህል ብዙ ወጣቶች ሲጋራ ማጨስ እንደ ዐዋቂ ወይም በዕድሜ እንደበሰሉ እንደሚያስቆጥራቸው በማሰብ ሰውነታቸውን በሲጋራ ይበክላሉ። ከዚህ የተነሳ አብዛኞቹ በኋለኛው ሕይወታቸው በልብ በሽታ፣ በሳንባ ካንሰር ወይም በሌላ ዓይነት የሳንባ በሽታ መሰቃየታቸው ምንኛ ያሳዝናል!
ውሳኔዎቻችንና ድርጊቶቻችን የሚያስከትሉብንን ውጤቶች ትኩረት ሰጥተን ማመዛዘናችን አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል” ብሎ የጻፈበት ጥሩ ምክንያት ነበረው።—ገላትያ 6:7, 8