ለመጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ትርጓሜ በምን ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት?
“መተርጎም” ለሚለው ቃል የተሰጠው አንደኛው ፍቺ “በግለሰቡ እምነት፣ ግምት ወይም ሁኔታ መሠረት መረዳት” የሚል ነው። (ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂዬት ዲክሺነሪ) በመሆኑም አንድ ሰው ለተለያዩ ነገሮች የሚሰጠው ትርጓሜ በተሞክሮው፣ በትምህርቱና በአስተዳደጉ ላይ የተመካ ነው።
ይሁንና ለመጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ትርጓሜ በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? የመጽሐፍ ቅዱስን ምንባቦች የራሳችንን “እምነት፣ አመለካከትና ሁኔታ” መሠረት በማድረግ የማብራራት ነፃነት አለንን? እርግጥ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና ተርጓሚዎች እንዲህ እንደማያደርጉ ከዚያ ይልቅ በአምላክ እንደሚመሩ ይናገራሉ።
ለዚህ የሚሆን አንዱ ምሳሌ ጆን ሊንጋርድ “ካቶሊክ” በሚል የብዕር ስም በ1836 ባሳተሙት ኤ ኒው ቨርሽን ኦቭ ዘ ፎር ጎስፕልስ በተባለው መጽሐፍ ላይ ለዮሐንስ 1:1 የተሰጠው የግርጌ ማስታወሻ ነው። እንዲህ ይላል:- “በማንኛውም እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች የግል አመለካከታቸውን የሚደግፍ ሐሳብ በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ እናገኛለን ብለው ያምናሉ። እንዲያውም በቅዱስ ጽሑፉ ከመመራት ይልቅ ለቅዱስ ጽሑፉ አገላለጽ የራሳቸውን ትርጉም ይሰጣሉ።”
ይህ ትክክለኛ አባባል ቢሆንም ጸሐፊው እንዲህ እንዲሉ ያነሳሳቸው ምን ነበር? ይህን የተናገሩት ለዚያ ጥቅስ ለሰጡት ትርጓሜ ድጋፍ እንዲሆናቸው ሲሉ ነበር። ጥቅሱን “በመጀመሪያ ‘ቃል’ ነበረ፤ ‘ቃልም’ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ‘ቃልም’ እግዚአብሔር ነበረ” በማለት የተረጎሙት ሲሆን ይህም የሥላሴን እምነት በግልጽ የሚደግፍ ነው።
ደራሲው የሥላሴን መሠረተ ትምህርት በሚደግፍ መንገድ ዮሐንስ 1:1ን እንዲተረጉሙ የገፋፋቸው ምን ነበር? እንዲህ እንዲያደርጉ ‘የመራቸው ቅዱስ ጽሑፉ’ ነውን? የሥላሴ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ላይ ስለማይገኝ ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ “ሥላሴ የሚል ቃልም ይሁን ግልጽ የሆነ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም” በማለት ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ የዬል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢ ዋሽበርን ሆፕኪንስ “በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስና ጳውሎስ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ . . . ስለዚህ መሠረተ ትምህርትም የተናገሩት ምንም ነገር የለም” ብለዋል።
ታዲያ ለዮሐንስ 1:1ም ሆነ ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የሚደግፍ ትርጓሜ ስለሚሰጡ ሰዎች ምን ብለን መደምደም እንችላለን? እንደ ሚስተር ሊንጋርድ አባባል ‘እነዚህ ሰዎች የሚመሩት በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ሳይሆን ለቅዱስ ጽሑፉ አገላለጽ የራሳቸውን ትርጉም በመስጠት ነው።’
ደስ የሚለው ነገር በዚህ ረገድ መመሪያ የሚሆነን የአምላክ ቃል አለልን። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጕም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:20, 21