ሥራና እረፍትን ሚዛናዊ ማድረግ
“እረፍት ጥሩ ልብስ ቢሆንም ዘወትር የሚለበስ ግን አይደለም።” ስሙ በውል የማይታወቅ አንድ ጸሐፊ የተናገረው ይህ አባባል የእረፍትን ዋጋማነት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። ይሁንና ከፍሬያማ ሥራ ጋር ሚዛናዊ መሆን እንዳለበትም ገልጿል።
በመንፈስ ተነሳሽነት መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈው ሰሎሞንም ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ ተናግሯል። ይህ ጥበበኛ ንጉሥ ልንርቃቸው ስለሚገቡን ሁለት ተቃራኒ ጽንፎች ጠቅሶ ተናግሯል። በመጀመሪያ “ሰነፍ እጁን ኮርትሞ ይቀመጣል፤ የገዛ ሥጋውንም ይበላል” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 4:5) አዎን፣ ሀኬተኛነት ሰውን ያደኸያል። ከዚህ የተነሣ ሰነፍ ሰው ጤናው አልፎ ተርፎም ሕይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ለሥራቸው ሲሉ ሁሉን ነገር የሚሠዉ ሰዎችም አሉ። ሰሎሞን የእነዚህን ሰዎች መቋጫ የሌለው ሩጫ “ከንቱ ነፋስንም እንደመከተል ነው” ሲል ገልጾታል።—መክብብ 4:4
በመሆኑም ሰሎሞን ሚዛናዊ ስለመሆን የሚናገርበት በቂ ምክንያት ነበረው:- “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል።” (መክብብ 4:6) አንድ ሰው ‘በድካሙ ደስ ሊለው’ ይገባል። ይህም ማለት ያገኘውን ነገር እያጣጣመ የሚደሰትበት ጊዜ ሊኖረው ይገባል። (መክብብ 2:24) ከሰብዓዊ ሥራ በተጨማሪ በሕይወታችን የምንሠራቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ከቤተሰባችንም ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ሊኖረን ይገባል። ሰሎሞን ተቀዳሚ ግዴታችን እንደሆነ አድርጎ የጠቀሰው ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት እንጂ ሰብዓዊ ሥራን አይደለም። (መክብብ 12:13) ስለ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች መካከል አንተም ትገኝበታለህ?