መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ሊጠቅመን ይችላልን?
“ከጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መነበብ የሚገባው 1 ከመቶ የሚሆነው ብቻ ነው። የተቀረው ምንም የማይጠቅምና ጊዜ ያለፈበት ነው።” ይህን የተናገረው አንድ ወጣት ነው። ብዙዎች በዚህ ወጣት አባባል ይስማሙ ይሆናል። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በመላው ዓለም በብዛት በመሸጥ ረገድ የመጀመሪያውን ደረጃ እንደያዘ የሚገኝ ቢሆንም ብዙዎች ጨርሶ ትኩረት አይሰጡትም፤ ምን ምን ትምህርቶችን እንደያዘም አያውቁም።
ዙዶይቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ በ1996 ባወጣው የገና ዕለት እትሙ “የመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መጥቷል። የተፈጥሮ ሳይንስና ዓለማዊ አስተሳሰብ በገነነበት ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ለብዙዎች የማይዋጡና ለመረዳት አዳጋች ይሆኑባቸዋል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። በዚህ ረገድ የተደረጉ ጥናቶችም ቢሆኑ ይህን ሪፖርት የሚያጠናክሩ ናቸው። ብዙዎቹ ልጆች ኢየሱስ በትክክል ማን እንደሆነ እንኳ እንደማያውቁ አንዳንድ ጥናቶች አጋልጠዋል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ስለ ኮብላዩ ልጅና ስለ ሳምራዊው ጎረቤት የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መተረክ የቻሉት ከግማሽ የሚያንሱ ሰዎች ናቸው።
የስዊስ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ያሳተመው ሪፎርሜርቴ ፎረም የተባለው ጽሑፍ በስዊዘርላንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተፈላጊነት ከበፊቱ እየቀነሰ እንደመጣ ገልጿል። በቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ በመጻሕፍት መደርደሪያቸው ላይ ተቀምጦ አቧራ ከመጠጣት በቀር ምንም የፈየደላቸው ነገር የለም። በብሪታንያ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኞቹ ሰዎች ቤት የሚገኝ ቢሆንም ብዙዎቹ አንብበውት እንደማያውቁ አንድ ጥናት አመልክቷል።
በአንጻሩ ደግሞ በዓለም ዙሪያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አመለካከት ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስን የአምላክ ቃል እንደሆነ እንዲሁም ከፍ ያለ ዋጋና ጥቅም እንዳለው አድርገው ይመለከቱታል። ስለሆነም ዘወትር ያነብቡታል። አንዲት ወጣት እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች:- “በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን ለማንበብ ጥረት አደርጋለሁ። ይህም እርካታ ይሰጠኛል።” እንዲህ ያሉ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ለሚሰጠው ትምህርት ትኩረት ከመስጠታቸውም በላይ ምክሩን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ። በችግር በተሞላው በዛሬው ዓለም ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅማቸው እንደሚችል ያምናሉ።
የአንተስ አመለካከት ምንድን ነው? በዚህ በሰለጠነው ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን የምትመለከተው እንደ ተራ መጽሐፍ አድርገህ ነው? ወይስ ከፍ ያለ ዋጋና ጥቅም እንደሚያስገኝ አድርገህ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ሊጠቅመን ይችላልን?