‘ነፋስ ሲታገለን’
ወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የገሊላን ባሕር በጀልባ ለመሻገር ሲታገሉ ስላጋጠማቸው ነገር ሲናገር ‘ከወደፊታቸው በሚነፍሰው ነፋስ ምክንያት መቅዘፍ ተቸግረው ተጨንቀው’ እንደነበር ገልጿል። ኢየሱስ ገና የባሕሩ ዳርቻ ላይ እንዳለ ጭንቀታቸውን ተመልክቶ በተአምር በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ ሄደ። ወደ ጀልባውም ገብቶ ከእነርሱ ጋር በሆነ ጊዜ ነፋሱ ቆመ።—ማርቆስ 6:48-51
ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከዚህ ቀደም ሲልም ‘ብርቱ ዐውሎ ነፋስ የተነሣበት’ አጋጣሚ እንደነበር ዘግቧል። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ “ነፋሱን ገሠጸው . . . ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ።”—ማርቆስ 4:37-39
ምንም እንኳ እኛ ዛሬ እንደዚህ ዓይነት ተአምራዊ ክስተቶች ሲከናወኑ የማየት አጋጣሚ ባናገኝም ከእነዚህ ክንውኖች ብዙ መማር እንችላለን። አደገኛ በሆነ ጊዜ ውስጥ የምንኖር ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የመከራ ነፋስ ያጋጥመናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲያውም በግል በሚደርሱብን ፈተናዎች ምክንያት የሚያጋጥመን ጭንቀት አንዳንድ ጊዜ የማዕበል ያህል ጠንካራ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም እፎይታ ማግኘት እንችላለን! ኢየሱስ የሚከተለውን ግብዣ አቅርቦልናል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።”—ማቴዎስ 11:28
‘የሚታገለን ነፋስ’ እንዳለ ሲሰማን በልባችን ‘ታላቅ መረጋጋት’ ማግኘት የምንችልበት መንገድ አለ። እንዴት? ይሖዋ አምላክ በሰጣቸው ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በተረጋገጠው ተስፋዎች ላይ እምነት በማሳደር ነው።—ከኢሳይያስ 55:9-11፤ ከፊልጵስዩስ 4:5-7 ጋር አወዳድር።