ቀለበታቸውን መልሰው እንዲያጠልቁ አድርጓቸዋል
“ጣቶቼን ተመልከቺ። ምን የተለየ ነገር ታያለሽ?” አንድ ሰውዬ የይሖዋ ምሥክር ለሆነች አንዲት ሴት እጁን አሳያት። እሷም እጁን ተመልክታ የጋብቻ ቀለበቱ ጣቱ ላይ እንደሌለ ወዲያውኑ አስተዋለች። እርሱና ሚስቱ ተስማምተው መኖር ጭራሽ ስላቃታቸው ለመፋታት እንደወሰኑ ነገራት። ምሥክሯ “መፋታት የለባችሁም!” አለችው። “ይህን መጽሐፍ ወስደህ አንብበው። ትዳራችሁን እንድታስተካክሉ ይረዳችኋል።” ይህን ተናግራ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ሰጠችው።a
ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰውዬው ደስተኛ ሆኖ ወደዚች ምሥክር መጣ። እጁን አሳያት። በዚህ ጊዜ የጋብቻ ቀለበቱ ጣቱ ላይ ነበር። እርሱና ሚስቱ እውቀት መጽሐፍን እንዳነበቡና አሁን በጣም ደስተኞች እንደሆኑ ነገራት። ቃል በቃል መጽሐፉ ቀለበታቸውን መልሰው እንዲያጠልቁ አድርጓቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው እውነተኛ ፍቅር እንዲያሳዩ ሊረዳቸው ይችላል። ይህ የሆነበት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ የተናገረው ፈጣሪያችን ራሱ ስለሆነ ነው።—ኢሳይያስ 48:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።