ክርስቲያናዊ ፍቅር በቃላት ብቻ የተወሰነ አይደለም
በትሪኒዳድ የሚገኘው የበርቶሎሜዩ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በእሳት በተቃጠለበት ጊዜ የቤተሰቡ አባላት ከሕይወታቸው በቀር የተረፈላቸው ምንም ነገር አልነበረም። በአቅራቢያቸው የምትኖር አንዲት ዘመዳቸው አስጠጋቻቸው። ታሪኩ ግን በዚህ አላበቃም።
ኦሊቭ በርቶሎሜዩ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ስትሆን ይህ ሁኔታ ሲደርስባት እርሷ የምትገኝበትን ጉባኤ አባላት ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እሷና ቤተሰቧ የተቃጠለባቸውን ቤት መልሰው ለመገንባት ገንዘብ ማዋጣት ጀመሩ። ከዚያም የግንባታ ሥራውን በበላይነት የሚቆጣጠር አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ግንባታው ተጀመረ። በቦታው ወደ 20 የሚጠጉ ምሥክሮችና አንዳንድ ጎረቤቶቻቸው ተገኝተው ነበር። ትንንሽ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ በሥራው የተካፈሉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ቀለል ያሉ ምግቦች በማዘጋጀት ረድተዋል።
የትሪኒዳዱ ሰንደይ ጋርዲያን እንደዘገበው ኦሊቭ “ቤተሰቤ በጥልቅ ተነክቷል” በማለት ተናግራለች። “ቤተሰቦቼ የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። ባለቤቴ ባየው ነገር እስከ አሁን እንደተገረመ ነው።”
የግንባታ ፕሮጀክቱ አስተባባሪ ስለተደረገው ጥረት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ በእርግጥም እንዲህ ያሉት ተግባራት የእውነተኛ ክርስትና መለያ ምልክቶች መሆናቸውን በአጽንኦት ተናግሯል። “ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ስለ ፍቅር ማውራት ብቻ አይደለም። የምንሰብከውን በተግባር ለማሳየት እንጥራለን” ሲል ገልጿል።—ዮሐንስ 13:34, 35
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኦሊቭ በርቶሎሜዩ ከባለቤቷ ጋር