“ይሄ ያሳምምህ ይሆናል”
እነዚህን ቃላት ከአሁን በፊት ሰምተሃቸው ታውቃለህ? ምናልባት አንድ ዶክተር ወይም ነርስ የታዘዘልህን ሕክምና ከመስጠታቸው በፊት እንደዚያ ብለውህ ያውቁ ይሆናል።
ሊያስከትል የሚችለውን ሥቃይ በመፍራት ብቻ ሕክምናውን አልቀበልም እንዳላልክ የታወቀ ነው። ከዚያ ይልቅ የተሻለ ጤንነት ለማግኘት ስትል ሥቃዩን ትችለዋለህ። ከበድ ባሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ሥር አንድን የሚያሠቃይ ሕክምና መቀበል ወይም አለመቀበል የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሊሆን ይችላል።
ሁልጊዜ የሕክምና ባለሞያ እርዳታ የሚያስፈልገን ባይሆንም እንኳን ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ተግሣጽ ወይም እርማት መቀበል ያስፈልገናል፤ አንዳንድ ጊዜም የሚሰጠን ተግሣጽ የማያስደስተን ሊሆን ይችላል። (ኤርምያስ 10:23) ልጆች እንዲህ ያለው ተግሣጽ እንደሚያስፈልጋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቃታል” ይላል።—ምሳሌ 22:15
እዚህ ላይ የተገለጸው በትር የወላጆችን ሥልጣን ያመለክታል። አብዛኞቹ ልጆች ተግሣጽ እንደማይወዱ እሙን ነው። ተግሣጹ አንድ ዓይነት ቅጣትን የሚጨምር ከሆነ ለመቀበል ያንገራግሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጥበበኛና አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ከልጆቹ ጊዜያዊ የስሜት መጎዳት ይልቅ ለዘለቄታው በሚያስገኝላቸው ጥቅም ላይ ያተኩራሉ። ክርስቲያን ወላጆች “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል” የሚለው የአምላክ ቃል ትክክለኛ መሆኑን ይገነዘባሉ።—ዕብራውያን 12:11፤ ምሳሌ 13:24
እርግጥ ነው ተግሣጽ የሚያስፈልጋቸው ልጆች ብቻ አይደሉም። ትልልቅ ሰዎችም ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ትልልቅ ሰዎችን በማስመልከት “ተግሣጽን ያዝ፣ አትተውም፤ ጠብቀው፣ እርሱ ሕይወትህ ነውና” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 4:13) አዎን፣ ብልህ የሆኑ ወጣቶችም ሆኑ ትልልቅ ሰዎች የኋላ ኋላ ሕይወታቸውን ስለሚታደግላቸው በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን ተግሣጽ ይቀበላሉ።