የአንባብያን ጥያቄዎች
አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት ከጉባኤው ጋር የጌታ እራትን ማክበር ባይችል ምን ዝግጅት ሊደረግ ይችላል?
አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምናልባትም የአልጋ ቁራኛ በመሆኑ ምክንያት ጉባኤው የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል ሲያከብር መገኘት ባይችል ሁኔታውን ግምት ውስጥ በማስገባት አንድ ነገር ማድረግ ይቻላል፤ ደግሞም መደረግ አለበት። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ክርስቲያን የዚያኑ ዕለት ምሽት ምሳሌያዊውን ቂጣና ወይን ለወንድም እንዲወስድለት ዝግጅት ማድረግ ይችላሉ።
ቂጣውንና ወይኑን የሚወስድለት ሽማግሌ ወይም ሌላ ወንድም እንደ አመቺነቱ አጠር ያለ ሐሳብ ሊያካፍለውና በዓሉን በሚመለከት አንዳንድ ጥቅሶች ሊያነብለት ይችላል። ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ያደረገውን እንደ ምሳሌ መከተል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 26:26ን ሊያነብለት ይችላል፤ ከዚያም ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያልቦካውን ቂጣ ያቀርብለታል። ቀጥሎ ደግሞ ማቴዎስ ምዕራፍ 26 ቁጥር 27ና 28ን አንብቦ በድጋሚ ጸሎት ካደረጉ በኋላ ወይኑን ሊያቀርብለት ይችላል። ቂጣውና ወይኑ ምንን እንደሚያመለክቱ አጠር ያሉ ሐሳቦችን ማከል የሚቻል ሲሆን የመደምደሚያ ጸሎት ማቅረባቸው ተገቢ ነው።
እርግጥ ነው፣ ጉባኤው የጌታ እራት በዓልን በሚያከብርበት ወቅት በቦታው ለመገኘት ማንኛውም ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን በጠና በመታመሙ፣ ሆስፒታል በመግባቱ ወይም በሌሎች ከአቅም በላይ በሆኑ ሁኔታዎች የተነሳ ኒሳን 14 ዕለት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር የማይችል ከሆነስ? እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመው ቅቡዕ ክርስቲያን በሙሴ ሕግ ውስጥ የሰፈረውን ሥርዓት በመከተል ከ30 ቀን በኋላ በዓሉን በግሉ ሊያከብር ይችላል።—ዘኍልቍ 9:9-14