ድሆችን የሚጠቅም እርዳታ
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ድሆችን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ ያከናወነውን አገልግሎት በተመለከተ አንድ የዓይን ምሥክር “ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል” ሲል ጽፏል። (ማቴዎስ 11:5) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉትን በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ድሆች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ለእነርሱ የሚሆን ምስራች ይኖር ይሆን? አዎን፣ ተስፋ ያዘለ መልእክት አለ!
በጥቅሉ ሲታይ ዓለም ድሆችን ችላ የሚል ቢሆንም እንኳ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፣ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (መዝሙር 9:18) በሰማይ ያለው እውን መስተዳድር ማለትም የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ አገዛዝን በሙሉ አስወግዶ መግዛት ሲጀምር እነዚህ አጽናኝ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። (ዳንኤል 2:44) በሰማይ ያለው የዚህ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ “ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።”—መዝሙር 72:13, 14
ክርስቶስ ምድርን ሲገዛ የሰዎች ኑሮ ምን መልክ ይኖረው ይሆን? ክርስቶስ በሚገዛው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በድካማቸው ፍሬ ይደሰታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በሚክያስ 4:3, 4 ላይ እንዲህ ይላል:- “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።” የአምላክ መንግሥት በሽታንና ሞትን ጭምር ያስወግዳል። (ኢሳይያስ 25:8) ምንኛ የተለየ ዓለም ይሆናል! እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ያስጻፈው አምላክ ራሱ በመሆኑ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ተስፋ ያዘለ ከመሆኑም ሌላ በድህነት ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ራስን ዝቅ አድርጎ የመመልከት ችግርን ጨምሮ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች እንድንቋቋም ይረዳናል። አንድ ችግረኛ የሆነ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በሚያጠናበት ጊዜ አምላክ ባለጠጋን ከድሀ አስበልጦ እንደማያይ ይገነዘባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ‘እነርሱ ሁሉ የእጁ ሥራ ናቸውና [አምላክ] ባለጠጋውን ሰው ከድሀው ይበልጥ አይመለከትም’ በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 34:19) አምላክ ባለጠጋንም ሆነ ድሀን እኩል ይወድዳል።—ሥራ 10:34, 35