ለኖኅ የተጻፈ ደብዳቤ
“ውድ ኖኅ፣ የአንተን ታሪክና ከቤተሰብህ ጋር ከጥፋት ውኃ የተረፋችሁበትን መርከብ እንዴት እንደሠራኸው የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በተደጋጋሚ አንብቤዋለሁ።”
ሚናማሪያ የተባለች የ15 ዓመት ወጣት እድሜያቸው ከ14-21 ዓመት የሆኑ ተማሪዎች ለሚሳተፉበት የሥነ ጽሑፍ ውድድር የላከችው ደብዳቤ ከላይ ባሉት ቃላት ይጀምራል። ውድድሩን ያዘጋጁት የፊንላንድ የፖስታ አገልግሎት፣ የፊንላንድ የአፍ መፍቻ ቋንቋ መምህራን ፌዴሬሽን እና የፊንላንድ የሥነ ጽሑፍ ማኅበር በጋራ በመተባበር ነበር። ውድድሩ በአንድ መጽሐፍ ላይ ተመሥርቶ ደብዳቤ መጻፍ ሲሆን ደብዳቤው የሚጻፍለት ሰው የመጽሐፉ ደራሲ ወይም በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኝ አንድ ገጸ ባሕርይ ሊሆን ይችላል። መምህራኑ ከተማሪዎቻቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ከ1,400 የሚበልጡትን መርጠው ለውድድሩ ዳኞች አስተላለፉ። ከዚያም ዳኞቹ አንደኛ የወጣውን ደብዳቤ፣ ሁለተኛ ደረጃ ያገኙትን አሥር ደብዳቤዎችና ሦስተኛ ደረጃ ያገኙትን ሌሎች አሥር ደብዳቤዎች መረጡ። ሚናማሪያ ደብዳቤዋ ሦስተኛ ደረጃ በማግኘቱ በጣም ተደስታለች።
በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኘው ሚናማሪያ የዛሬ 5,000 ዓመት ገደማ ለኖረው ለኖኅ ደብዳቤ ለመጻፍ የመረጠችው ለምን ነበር? እንዲህ ትላለች:- “ወደ አእምሮዬ የመጣው የመጀመሪያው መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ገጸ ባሕርያት በሚገባ አውቃቸዋለሁ። ስለ እነርሱ በጣም ብዙ ጊዜ ስላነበብኩ ለእኔ ልክ በሕይወት እንዳሉ ያህል ናቸው። ኖኅን የመረጥኩት ደግሞ ሕይወቱ ከእኔ ፈጽሞ የተለየና ትኩረት የሚስብ ስለነበረ ነው።”
ሚናማሪያ ለኖኅ የጻፈችውን ደብዳቤ የደመደመችው በሚከተሉት ቃላት ነው:- “እስካሁን ድረስ በእምነትህና በታዛዥነትህ አርአያ የምትሆን ነህ። ያሳለፍከው ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡ ሁሉ እምነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ነው።”
የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ የሆነች አንዲት ወጣት የጻፈችው ይህ ደብዳቤ መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያውና” ወጣት አረጋዊ ሳይል በሁሉም ሰዎች ላይ “የሚሠራ” መሆኑን በሚገባ ያሳያል።—ዕብራውያን 4:12