“የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የያዘ የመጀመሪያው ጽሑፍ”
ከሃያ አምስት ዓመት በፊት እስራኤላውያን አርኪኦሎጂስቶች በጣም አስገራሚ የሆነ የቁፋሮ ውጤት አገኙ። በኢየሩሳሌም፣ በሄኖም ሸለቆ ተዳፋት አካባቢ በሚገኝ የመቃብር ዋሻ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በላያቸው የተቀረጹባቸው ሁለት ትናንሽ ከብር የተሠሩ ጥቅልሎችን አገኙ። ጥቅልሎቹ የተጻፉት ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎናውያን ከመጥፋቷ በፊት ነበር። በላያቸው የተጻፈው ጥቅስ በዘኍልቍ 6:24-26 ላይ ሠፍሮ ከሚገኘው ቡራኬ የተወሰደ ነው። በሁለቱም ጥቅልሎች ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። እነዚህ ጽሑፎች “ከዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰዱ ጥቅሶችን የያዙ ከጥንቱ ዓለም የተገኙና በጣም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶች” ተብለዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ምሁራን ጥቅልሎቹ ተጽፈዋል ተብሎ የሚታመንበትን ዓመት የማይቀበሉ ከመሆኑም ሌላ የተጻፉት በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው በማለት ይከራከራሉ። ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ የእነዚህ ሁለት በጣም ትናንሽ ጥቅልሎች የመጀመሪያው ፎቶግራፍ ዝርዝር ጉዳዮችን አቅርቦ ለማየት የሚያስችል ጥራት የሌለው መሆኑ ነው። ቀኑን አስመልክቶ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት አንድ የምሁራን ቡድን አዲስ ጥናት ማካሄድ ጀመረ። ምሁራኑ ከፍተኛ ጥራት ያለውን የጥቅልሎቹን ዲጂታል ምስል ማግኘት እንዲችሉ በጣም ዘመናዊ የሆነውን የዲጂታል ፎቶግራፍ ጥበብና ምስሉን በኮምፒውተር ለማየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተጠቀሙ። የዚህ አዲስ ጥናት ውጤት በቅርቡ ይፋ ሆኗል። ታዲያ ይህ የምሁራን ቡድን ምን መደምደሚያ ላይ ደረሰ?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአርኪኦሎጂያዊ ጥናት የተገኘው መረጃ ጥቅልሎቹ የተጻፉት ከባቢሎን ግዞት በፊት መሆኑን እንደሚያሳይ ምሁራኑ አበክረው ገልጸዋል። የፊደላቱን ቅርጽ፣ አጣጣል፣ አቀማመጥና ፊደላቱ የተቀረጹባቸውን የመስመሮች ቅደም ተከተል እንዲሁም የተጻፉበትን አቅጣጫ በመመልከት ጥቅልሎቹ የተጻፉት ተመሳሳይ በሆነ ወቅት ላይ ማለትም በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መገባደጃ አካባቢ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በመጨረሻም የፊደላቱን ቅርጽና አጣጣል በማየት ቡድኑ የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሷል:- “ጽሑፎቹ የተቀረጹበትን ጊዜ በተመለከተ ጥቅልሎቹ ላይ የሚታየው የፊደላት ቅርጽና አጣጣል የሚገልጸው ሐቅ በአርኪኦሎጂያዊና በጥንታዊ ጽሑፎች ላይ በሚካሄድ ጥናት ከተገኘው ማስረጃ ጋር የሚጣጣም ነው።”
ቡሌቲን ኦቭ ዚ አሜሪካን ስኩልስ ኦቭ ኦሪየንታል ሪሰርች የተባለው መጽሔት ከቲፍ ሂኖም በሚል ስያሜም ስለሚታወቁት ስለ እነዚህ የብር ጥቅልሎች እንዲህ በማለት ገልጿል:- “በእነዚህ ጥቅልሎች ላይ ተቀርጾ የሚገኘው ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የያዘ የመጀመሪያው ጽሑፍ መሆኑን በተመለከተ አብዛኞቹ ምሁራን የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።”
[Credit Lines]
ዋሻ:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.; ጽሑፎቹ:- Photograph © Israel Museum, Jerusalem; courtesy of Israel Antiquities Authority