የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w06 7/15 ገጽ 32
  • “ከዛሬ ጀምሮ አምላክ መኖሩን አምኛለሁ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ከዛሬ ጀምሮ አምላክ መኖሩን አምኛለሁ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
w06 7/15 ገጽ 32

“ከዛሬ ጀምሮ አምላክ መኖሩን አምኛለሁ”

በፕራግ፣ ቼክ ሪፑብሊክ የምትኖር አሊክሳንድራ የተባለች ዩክሬናዊት ከሥራ ወደ ቤቷ እየተመለሰች ሳለ በአውቶቡስ ማቆሚያ አካባቢ መሬት ላይ የወደቀ አነስተኛ ቦርሳ በእግረኞች ሲረጋገጥ ተመለከተች። ቦርሳውን ከወደቀበት አንስታ ስትከፍተው ዓይኗን ማመን አልቻለችም። በቦርሳው ውስጥ አንድ ላይ የታሠሩና ብዛት ያላቸው ባለ 5,000 ኮሩና ኖቶች ነበሩ! አጠገቧ ካሉት ሰዎች መካከል ማንም ቦርሳው ጠፍቶበት እየፈለገ ያለ አይመስልም። አሊክሳንድራ በቼክ ሪፑብሊክ ውስጥ የምትኖር የውጭ አገር ዜጋ እንደመሆኗ መጠን ኑሮ ከብዷት ነበር። ታዲያ ምን ታደርግ ይሆን?

አሊክሳንድራ ቤቷ እንደተመለሰች ቦርሳውን ለልጇ ለቪክቶሪያ አሳየቻት። የባለቤቱን ስምና አድራሻ ቦርሳው ውስጥ ቢፈልጉም ሊያገኙት አልቻሉም። ሆኖም በርከት ያሉ ቁጥሮች የተጻፉበት አንድ ትንሽ ወረቀት ቦርሳው ውስጥ አገኙ። በወረቀቱ በአንደኛው በኩል የባንክ የሒሳብ ቁጥር የተጻፈበት ሲሆን በሌላው በኩል ደግሞ በርካታ ቁጥሮች ተጽፈው ነበር። ቦርሳው ውስጥ እዛው አገር የሚገኝን ባንክ የሚጠቁም ሐሳብና “330,000 ኮሩኒ” (10,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ) የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ወረቀት ነበር። በቦርሳው ውስጥ ያገኙት ገንዘብ በወረቀቱ ላይ ከሰፈረው ጋር እኩል ነበር።

አሊክሳንድራ የባንኩ ስልክ ይሆናል ብላ ባሰበችው ቁጥር ለመደወል ብትሞክርም ሊሳካላት አልቻለም። በመሆኑም እሷና ልጇ ባንኩ ድረስ በመሄድ ሁኔታውን አስረዱ። በቦርሳው ውስጥ ስላገኙት የሒሳብ ቁጥርም ጠየቁ። ሆኖም ቁጥሩ በባንኩ ውስጥ እንዳልተመዘገበ ተነገራቸው። በሚቀጥለው ቀን አሊክሳንድራ በቦርሳው ውስጥ ያገኘችውን ሌላ ቁጥር ይዛ ወደ ባንኩ ተመልሳ ሄደች። እውነትም፣ የዚህ ሒሳብ ቁጥር ባለቤት የሆነችው ሴት የባንኩ ደንበኛ ነበረች። አሊክሳንድራና ልጇ ቪክቶሪያ የቦርሳው ባለቤት የሆነችውን ሴት አገኟት፤ እሷም ቦርሳዋ እንደጠፋባት አረጋገጠችላቸው። በመጨረሻም ሁሉም ከተገናኙና ሴትየዋ በጣም ካመሰገነቻቸው በኋላ “ብሩን እንድትመልሱልኝ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል?” በማለት ጠየቀቻቸው።

ቪክቶሪያም “ምንም የምንጠይቅሽ ነገር የለም። ገንዘብ ብንፈልግ ኖሮ፣ ልንወስደው እንችል ነበር” አለቻት። ቪክቶሪያ የቼክን ቋንቋ አቀላጥፋ መናገር ባትችልም እንዲህ በማለት ልታስረዳት ሞከረች:- “ብሩን የመለስንልሽ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆንን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን የራሳችን ያልሆነውን ነገር እንድንወስድ አይፈቅድልንም።” (ዕብራውያን 13:18) ሴትየዋም “ከዛሬ ጀምሮ አምላክ መኖሩን አምኛለሁ” በማለት በደስታ ተናገረች።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ