“የጥያቄ ሳጥን
◼ የማኅበሩን ጽሑፎች አባዝቶ ለሌሎች ማሰራጨት ተገቢ ነውን?
ባለፉት ዓመታት ማኅበሩ በጣም ብዙ ዓይነት ጽሑፎችን አውጥቷል። እነዚህም ጽሑፎች እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ የእውቀት ዘርፍ የሚዳስሱ ናቸው ለማለት ይቻላል። በቅርብ ዓመታት እውነትን የተማሩ ግለሰቦች በፊት ከታተሙትና በአሁኑ ጊዜ በማኅበሩ በኩል ሊገኙ ከማይችሉት ጽሑፎች የሚገኘው ጥቅም እንዳመለጣቸው ሊሰማቸው ይችላል። አንዳንዶች የድሮዎቹን ጽሑፎች ቅጂዎች ለማግኘት ሲሉ ብዙ ደክመዋል። ሌሎች ደግሞ የድርጅቱን ጽሑፎች ራሳቸው እንደገና ለማባዛትና በተለያዩ መንገዶች ማንም ሰው ሊያገኛቸው እንዲችል ለማድረግ የራሳቸውን እርምጃ ወስደዋል። ይህም ጽሑፎቹን እንደገና ማተምንና በኮምፒዩተር ገልብጦ ማባዛትን ይጨምራል። አንዳንዶች እንዲህ የሚያደረጉት የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ነው።
ታማኙ “ባሪያ” በመንፈሳዊ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለሚያውቅ “በተገቢው ጊዜ” ያቀርብልናል። (ማቴ. 24:45 አዓት) በፊት የታተሙ ጽሑፎችን እንደገና ማተም በሚያስፈልግበት ጊዜ ማኅበሩ ይህንን ለማድረግ ዝግጅቶችን አድርጓል። ለምሳሌ ያህል ከ1960 እስከ 1985 የወጡት የመጠበቂያ ግንብ ጥራዞች (ባውንድ ቮልዩምስ) እንደገና ታትመው ሁሉም ሰው ሊያገኛቸው እንዲችል ተደርጓል። ይሁን እንጂ ግለሰቦች እንዲህ ያሉትን ጽሑፎች እንደገና ራሳቸው ማተምና ማሰራጨት ከጀመሩ አላስፈላጊ የሆኑ ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ።
እነዚህ ጽሑፎች የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ሲባል እንደገና በሚታተሙበትና በሚሰራጩበት ወቅት ከባድ ችግሮች ተፈጥረዋል። በሐምሌ 1977 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣው የጥያቄ ሣጥን እንዲህ ብሏል:- “በመንግሥት አዳራሽ፣ የመጽሐፍ ጥናት በሚከናወንባቸው ቦታዎችና በይሖዋ ሕዝቦች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የንግድ ጥቅም ለማግኘት ስንል ማናቸውንም የዕቃ ወይም የአገልግሎት ሽያጭ በመጀመር ወይም ማስታወቂያ በመናገር ቲኦክራቲካዊ ቅርርባችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ባንጠቀምበት በጣም የተሻለ ነው። ይህም መንፈሳዊ ጉዳዮች ሊኖራቸው የሚገባቸውን ቅድሚያ እንዲያገኙና የንግድ ሥራዎችም ተገቢ ቦታቸውን እንዲይዙ ለማድረግ ይረዳል።” ስለዚህ በአምላክ ቃል ወይም ከእርሱ ጋር በተያያዙ ነገሮች ነግደን ትርፍ ከመፈለግ መቆጠባችን አስፈላጊ ነው።