የጥያቄ ሣጥን
◼ አንድ ሰው በሚጠመቅበት ጊዜ ምን ዓይነት ልብስ ቢለብስ ተገቢ ይሆናል?
ምንም እንኳን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያለው የአለባበስ ሥርዓት ቢለያይም መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር’ እንዲለብሱ የሚሰጠው ማሳሰቢያ በየትም ቦታ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚሠራ ነው። (1 ጢሞ. 2:9) ለጥምቀት ተገቢ የሚሆነውን ልብስ በተመለከተ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ልንሠራበት ይገባል።
የሰኔ 1, 1985 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ በገጽ 30 ላይ ለመጠመቅ እየተዘጋጀ ላለ ሰው የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ለጥምቀት በምንጠቀምባቸው የዋና ልብስ ዓይነቶች ላይ ልከኝነት ጎልቶ መታየት አለበት። በተለይ የፋሽን ሞዴል አውጪዎች ለኃፍረተ ሥጋ የተጋነነ ትኩረት ለመስጠት የሚፈልጉ በሚመስሉበትና ራቁት ከመሆን ምንም ያልቀረው አለባበስን እስከማውጣት በደረሱበት በአሁኑ ጊዜ ልከኝነት አስፈላጊ ነው። ግምት ውስጥ ልናስገባው የሚያስፈልገው ሌላው ጉዳይ አንዳንድ ልብሶች ውኃ ሳይነካቸው ልከኛ መስለው ሊታዩና ውኃ ውስጥ ሲገቡ ግን እንደ መጀመሪያው ላይሆኑ እንደሚችሉ ነው። ማንኛውም ተጠማቂ ጥምቀትን በመሰለ ታላቅ ወቅት ላይ የሌሎችን ሐሳብ ወደ ሌላ ለማዞር ወይም ለመደናቀፊያ ምክንያት ለመሆን እንደማይፈልግ ግልጽ ነው። — ፊልጵስዩስ 1:10”
ከዚህ ምክር ጋር በመስማማት ተጠማቂዎች ሁሉ የጥምቀት ሥርዓቱን ታላቅነት በማሰብ ልከኛ ልብስ ለመልበስ ይፈልጋሉ። እንግዲያው በጣም አጭር የሆነ የዋና ልብስ ወይም ውኃ ውስጥ ሲገባ በአሣፋሪ ሁኔታ ሰውነት ላይ የሚጣበቅ ልብስ ለአንድ ክርስቲያን ተገቢ ስላልሆነ ሊለበስ አይገባም። በውኃው ላይ በቀላሉ ተንሣፍፈው የሚቀሩ በጣም ሰፋፊ ጉርድ ወይም ሙሉ ቀሚሶችን ከመልበስ ይልቅ ሰፊና አጭር ያልሆኑ ልከኛ ልብሶችን መልበሱ ይበልጥ ተገቢ ይሆናል። በተመሣሣይም አንድ ሰው የተዝረከረከ ወይም ያደፈ ልብስ ለብሶ መቅረቡም ተገቢ አይሆንም። ከዚህም በተጨማሪ ዓለማዊ ጽሑፎች ወይም የንግድ ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው ካናቴራዎች መልበሱ ተገቢ አይደለም።
የጥምቀት ጥያቄዎቹን እንዲጠይቁ የተመደቡት ሽማግሌዎች ከጥምቀት እጩው ጋር ጥያቄዎቹን በሚከልሱለት ጊዜ ይህ ተገቢ ልብስ የመልበሱን አስፈላጊነት ለመንገር ምቹ ጊዜ ይሆናል። በዚህ መንገድ የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ ክብር ይኖረዋል፤ እኛም ከዓለም የተለየን ሆነን መታየታችንን እንቀጥላለን። — ከዮሐንስ 15:19 ጋር አወዳድር።