“የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ጥቅም ማስፋት
1 የ1993 የዓመት መጽሐፍ በገጽ 26 እና 27 ላይ የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ስልጠና በሌሎች አገሮችም ለማስፋት ስለተደረገው ዝግጅት ሪፖርት አቅርቦ ነበር። በቅርቡ ትምህርቱ እየተሰጠባቸው ስላሉ ልዩ ልዩ አገሮች ስናነብ ደስ ብሎን ነበር። በዛምቢያ አዲሱ የቅርንጫፍ ሕንፃ በሚያዝያ ወር በተመረቀበት ወቅት በዚሁ አገር የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለመክፈት እየተደረጉ ስላሉት ዝግጅቶች ማስታወቂያ ተነግሯል። አሁን ደግሞ ትምህርት ቤቱ በኬንያና በሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በቅርቡ ማሰልጠን እንደሚጀምር ስናስታውቃችሁ በጣም ደስ ይለናል። በክልላችን የሚደረገው የአገልጋዮች ሥልጠና የመጀመሪያ ክፍል የሚካሄደው በናይሮቢ ነው። በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ለመሰልጠን የሚፈልጉ ተማሪዎች ምዝገባ የሚደረገው መጋቢት 3, 1994 ይሆናል።
2 በትምህርት ቤቱ ገብተው ለመሰልጠን የሚፈልጉ ነጠላ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በክልል ስብሰባ ጊዜ ከወረዳና ከክልል የበላይ ተመልካቾች ጋር በሚደረገው ስብሰባ ለመገኘት ይችላሉ። በዚህ ስብሰባ ላይ ስለ ትምህርት ቤቱ ዓላማና ተመዝግበው ለመሰልጠን ማሟላት ስለሚገባቸው አንዳንድ ብቃቶች ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉ።
3 ትምህርት ቤቱ በ1987 ተመርቆ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ቅርብ ዓመታት የዓመት መጽሐፉ ትምህርት ቤቱን በተመለከተ አጠር ያሉ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል። እነዚህ ሪፖርቶች በልዩ ልዩ አገሮችና ቋንቋዎች ትምህርቱን ለመስጠት የተወሰዱትን እርምጃዎች ይገልጻሉ። እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ተመርቀው የሚወጡት ወንድሞች የተሰጣቸውን ኃላፊነትና የሥራ ምድብ በሚገባ ለማከናወን በተሻለ ሁኔታ የታጠቁ መሆናቸውን ሪፖርቶቹ ገልጸዋል። አሁን በክልላችን ከአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚገኙትን ጥቅሞች ለማየት በተስፋ ልንጠባበቅ እንችላለን።