መለኮታዊ ትምህርት ኃይለኛ ግፊት ያሳድራል
1 መለኮት ከሆነው ፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ትምህርት የምናገኝ በመሆናችን እንዴት ታድለናል! (መዝ. 50:1፤ ኢሳ. 30:20) ዛሬ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ለመማር ወደ ይሖዋ ተራራ ማለትም ወደ ንጹሕ አምልኮው እየጎረፉ ናቸው። (ሚክ. 4:2) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የሰውን አስተሳሰብና ዓለማዊ ጥበብ ከፍ ከፍ በሚያደርጉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው ይማራሉ። ሆኖም ይሖዋንና በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን ችላ የሚል ጥበብ በአምላክ ዓይን ሞኝነት ነው፤ በዚህ ጥበብ የሚመሩ ሰዎችም ሞኞች ይሆናሉ። — መዝ. 14:1፤ 1 ቆሮ. 1:25
2 በቅርቡ ባደረግነው የወረዳ ስብሰባችን መለኮታዊው ትምህርት ያለውን ኃይል በተለየ መንገድ ለመገንዘብ ችለናል። “መለኮታዊ ትምህርት” የሚለው አጠቃላይ መልእክት በፕሮግራሙ ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ይስተጋባ ነበር። የአምላክ ቃል ከመንፈሱ ጋር በመሆን በዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት አንድ እንደሚያደርገን፣ ጠባያችንን እንደሚቀርጸው፣ ከአጋንንታዊ ትምህርቶች እንደሚጠብቀን እንዲሁም የተሻልን አገልጋዮች እንድንሆን እንደሚያሠለጥነን ተምረናል። አንተ በግልህ ከመለኮታዊ ትምህርት የተጠቀምከው እንዴት ነው?
3 በክርስቲያናዊ አኗኗር ላይ የሚያስከትለው ውጤት፦ መለኮታዊ ትምህርት ሕሊናችንን ለመቅረጽ ይረዳል። እያንዳንዱ ሰው የሚወለደው ሕሊና ኖሮት ቢሆንም በጽድቅ መንገድ ለመጓዝና ይሖዋን የሚያስደስት አገልግሎት ለማቅረብ ሕሊናችን እንዲመራን ከተፈለገ መሠልጠን አለበት። (መዝ. 19:7, 8፤ ሮሜ 2:15) በዓለም ያሉ ሰዎች አስተሳሰባቸውን በአምላክ ቃል መሠረት አልቀረጹትም። በዚህም ምክንያት ግራ ተጋብተዋል፤ እንዲሁም የቱ ትክክል የቱ ደግሞ ስህተት እንደሆነ እርግጠኞች አይደሉም። ሁሉም በየራሱ አስተሳሰብ ትክክለኛ መስሎ የሚታየውን ነገር ማድረጉን ስለሚቀጥል ግብረ ገብነትና ሥነ ምግባር የሚያጨቃጭቁ ጉዳዮች ሆነዋል። አብዛኛው ሕዝብ የራሱን የሕይወት ጎዳና ራሱ ለመወሰን እንዲችል ሙሉ ነፃነት ይፈልጋል። የእውነተኛውን ጥበብ ብቸኛ ምንጭ ለመስማት አይፈልግም። (መዝ. 111:10፤ ኤር. 8:9፤ ዳን. 2:21) መለኮታዊው ትምህርት ግን እንዲህ ላሉት አከራካሪ ጉዳዮች መፍትሔ ሰጥቶናል። በእርሱ ስለተማርንም የአምላክ ቤተሰቦች በመሆን በአንድነት እንኖራለን። በአገልግሎታችን ሥራ የበዛልን በመሆን ጥሩ ሕሊና ይዘን ወደፊት የሚመጣውን ነገር በትምክህት እንጠባበቃለን።
4 መለኮታዊ ትምህርት “በትምህርት ነፋስ ሁሉ” እንዳንወሰድ ይረዳናል። (ኤፌ. 4:14) ሰዎችን ስህተት ፈላጊዎችና ተጠራጣሪዎች እንዲሆኑ የሚያደርጋቸውና ሁሉን ነገር ራሳቸው እንዲወስኑ የሚያደፋፍራቸው እንዲሁም ወደ ሥነ ምግባር ውድቀት የሚመራቸው የፍልስፍና ትምህርት አይማርከንም። በይሖዋ የተማርን በመሆናችን ደስ ይለናል፤ ስለዚህም ብዙዎች ከሚያጋጥማቸው የልብ ሐዘን እንድናለን። የይሖዋ ሕግጋትና ማሳሰቢያዎች ‘ከበስተኋላችን’ ሆነው “መንገዱ ይህች ናት፤ በእርስዋም ሂድ” እንደሚል “ቃል” ናቸው። — ኢሳ. 30:21
5 ስብሰባዎቻችንና አገልግሎታችን፦ በዕብራውያን 10:23–25 ላይ ላይ ያለውን ቃል ከአምላክ እንደተሰጠ ትእዛዝ አድርገን እንመለከተዋለን። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚያስተምረን ይሖዋ ነው። ዘወትር በስብሰባዎች ላይ የመገኘት ልምድ አለን ወይስ ወደ ስብሰባዎች መሄድ እምብዛም ቅድሚያ የማንሰጠው ጉዳይ ነው? አንድ ላይ መሰብሰብ የአምልኳችን ክፍል መሆኑን አስታውስ። የምርጫ ጉዳይ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። ይሖዋ በመንፈሳዊ ሊመግበን ካዘጋጀልን ፕሮግራም አንዱም እንዲያመልጠን በጭራሽ አንፈልግም።
6 ሙሴ “ጥበበኛ ልብ እንዲኖረን ዘመናችንን እንዴት መቁጠር እንዳለብን አሳየን” ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል። (መዝ. 90:12 አዓት) ይህ የኛም ጸሎት ነውን? እያንዳንዱን ውድ ቀን እናደንቀዋለንን? የምናደንቅ ከሆነ እያንዳንዱን ቀን ለታላቁ አስተማሪያችን ለይሖዋ አምላክ ክብር በሚያመጣ ዋጋማ መንገድ በማሳለፍ “ጥበበኛ ልብ እንዲኖረን” እናደርጋለን።