መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ትካፈላለህን?
1 በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ከምናደርጋቸው ነገሮች መካከል በተወሰኑ ጊዜያት ስለ ይሖዋ ለሌሎች መናገር ይገኝበታል። መደበኛ በሆነ መንገድ ለመመሥከር ማለትም ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ጊዜ እንመድባለን። መደበኛ ባይሆኑም እንኳ ስለ እውነት ለሌሎች የምንናገርባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ። በዚህ መንገድ የሚሰጠውን ምሥክርነት መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት እንለዋለን።
2 አንዳንድ አስፋፊዎች በዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ለመሳተፍ ብዙ አጋጣሚዎችን አግኝተዋል። ሁላችንም ወደ ትልልቅ ስብሰባዎች ስንሄድና ከስብሰባዎቹ ስንመለስ፣ እረፍት ስንወስድና ዘመዶቻችንን ስንጠይቅ አጋጣሚዎቹን ነቅተን በመጠባበቅ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ጥረት ልናደርግ እንችላለን። እንዲህ ያለውን አጋጣሚ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ትጠቀምበታለህን?
3 አስቀድሞ እቅድ ማውጣት፦ አስቀድሞ የታሰበበት ዝግጅት ማድረግ ውጤታማ በሆነ መንገድ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። በዚህ ረገድ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት እንድንሰጥ የሚረዱን ልዩ ልዩ ጽሑፎች ስላሉ የተሟላ ዝግጅት አለን። ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች በተጨማሪ አእምሮን የሚያመራምር አቀራረብና ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ርዕሶች ያሏቸው ብዙ ትራክቶች አሉን። የተለያየ አስተዳደግ፣ የትምህርት ደረጃና ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች ስሜት የሚማርኩ ልዩ ልዩ ብሮሹሮች አሉ። ሰዎች ማወቅ የሚፈልጓቸውን ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች የሚመረምሩ በቀላሉ ለመያዝ ምቹ የሆኑ መጽሐፎችም አሉን። በየትኞቹ ጽሑፎች መጠቀም ተስማሚ ሆኖ አግኝተኸዋል? ይህን በቤተሰብ ደረጃ አስቡበት። ከዚያም ትክክለኛውን አጋጣሚ ስታገኙ ምን ብላችሁ እንደምትናገሩ ተለማመዱ።
4 ንግግር መጀመር የምንችለው እንዴት ነው?፦ ከአንድ ሰው ጋር ቀጠሮ ካለንና የቀጠርነውን ሰው ለመጠበቅ ጥቂት ጊዜ የምናጠፋ ሆኖ ከተሰማን፣ ከምናገኘው ሰው ጋር ለመወያየት እንድንችል በቅርብ ከወጡት መጽሔቶች በአንድ አስደሳች ርዕስ ላይ ልንዘጋጅና መጽሔቶቹን ይዘን ልንሄድ እንችላለን። አለዚያም በትራክት ወይም በብሮሹር ተጠቅመን ውይይት ለመጀመር እንችላለን። እንዲህ ባለው ጊዜ አንዳንድ አስፋፊዎች በወቅቱ በተደረገና የሰዎችን ትኩረት ስለሳበ ነገር አንድ ቃል መናገርና ከዚያም ስለ ጉዳዩ ምን እንደተሰማው ሰውዬውን መጠየቅ ውይይት ለመጀመር የሚያስችል ውጤታማ መንገድ ሆኖ አግኝተውታል። አንዳንዶች በወቅቱ የተከናወኑትን አንዳንድ ሁኔታዎች አስመልክቶ አእምሮን የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ሆኖ አግኝተውታል። ያም ሆነ ይህ የግል ተነሣሽነት ካለን አጋጣሚውን እንጠቀምበታለን።
5 መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በምንሰጥበት ጊዜ ሁሉ ሰውዬው የሚሰማውን የመግለጽ አጋጣሚ እንዲያገኝ መፍቀዱ ጥሩ ነው። ሁልጊዜ ትሕትናና አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። ሰውዬው የሚናገረውን በጥንቃቄ ካዳመጥን የሚያስደስቱት ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ከመቻላችንም በላይ መንፈሳዊ ጥሙን የሚያረኩ ቃላት እንናገራለን። (ምሳሌ 25:11) ከተቻለም በሌላ ጊዜ ተገናኝተን ፍላጎታቸውን ለመኮትኮት እንድንችል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ስምና አድራሻ መጻፍ ይኖርብናል። ለምሳሌ በናይሮቢ ተደርጎ በነበረው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ከልዩ ልዩ ቦታዎች የመጡ የስብሰባው ተካፋዮች ነበሩ። ከውጭ የመጡት ተሰብሳቢዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመሠከሩላቸው በአገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች ጽሑፎች እንዲላኩላቸውና ሰዎች ሄደው እንዲያነጋግሯቸው በመጠየቅ ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ልከዋል። በተጨማሪም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት በመስጠት ያሳለፍነውን ጊዜ በትክክል ሪፖርት ማድረግ እንችል ዘንድ መመዘገብ ይኖርብናል።
6 መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ችላ ብለን አናሳልፋቸው። ይህ የስብከት መንገድ ፍሬያማ ነው። የይሖዋ አገልጋዮችም መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ መካፈል ይኖርባቸዋል። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ለሰዎች ያለን ፍቅር በእያንዳንዱ አጋጣሚ እንድንናገር ያንቀሳቅሰን! — ማቴ. 5:14–16