በቅርብ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ
1 ኢየሱስ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቁ ሰው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ለደቀ መዛሙርቱም እንከን የማይወጣለት ምሳሌ ትቶላቸዋል። ምንም እንኳ ከእሱ የፍጽምና ደረጃ ጋር ለመተካከል ባንችልም ‘ፍለጋውን በቅርብ እንድንከተል’ ተመክረናል። (1 ጴጥ. 2:21) በቅንዓት እውነትን ለሌሎች በማካፈል በተቻለን መጠን ልክ እንደ ኢየሱስ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል።
2 ኢየሱስ ከሰባኪነት ደረጃ ከፍ ያለ ነበር፤ እርሱ ከሁሉ የላቀ አስተማሪም ነበር። “ሕዝቡ በትምህርቱ [“በማስተማር ጥበቡ” አዓት ] ተገረሙ” (ማቴ. 7:28) ኢየሱስ ይህን ያህል ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው? እስቲ ‘የማስተማር ጥበቡን’ ቀረብ ብለን እንመርምር።
3 ኢየሱስን እንዴት መከተል እንደምንችል፦ ኢየሱስ ከአባቱ የተማረ ነበር። (ዮሐ. 8:28) ዓላማውም ይሖዋን ማስከበርና ስሙን ከፍ ከፍ ማድረግ ነው። (ዮሐ. 17:4, 26) እኛም በምንሰብክበትም ሆነ በምናስተምርበት ጊዜ ዓላማችን ይሖዋን ለማስከበር እንጂ በምንም ዓይነት መንገድ የሰዎችን ትኩረት ወደ እኛ ለመሳብ መሆን የለበትም።
4 ኢየሱስ ያስተምረው የነበረው ነገር ሁሉ የተመሠረተው በአምላክ ቃል ላይ ነበር። ብዙ ጊዜ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቅስ ነበር። (ማቴ. 4:4, 7፤ 19:4፤ 22:31) እኛም አድማጮቻችንን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ልንመራቸው ይገባል፤ እንደዚህ ካደረግን የምንሰብከውም ሆነ የምናስተምረው ነገር ሁሉ የተመሠረተው በከፍተኛው ባለ ሥልጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሆነ እንዲያስተውሉ ልናደርጋቸው እንችላለን።
5 ኢየሱስ ባልተንዛዙ፣ ሊሠሩ በሚችሉና ባልተወሳሰቡ አገላለጾች ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ ያህል እንዴት የአምላክን ይቅርታ ልናገኝ እንደምንችል ሲገልጽ እኛም በበኩላችን ሌሎችን ይቅር እንድንል አበረታትቶናል። (ማቴ. 6:14, 15) የመንግሥቱን መልእክት በቀላልና ሊገባ በሚችል አገላለጽ ለማቅረብ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
6 ኢየሱስ የሰዎችን የማመዛዘን ችሎታ ለመቀስቀስ ሲል ምሳሌዎችንና ጥያቄዎችን በጥበብ ይጠቀም ነበር። (ማቴ. 13:34, 35፤ 20:20–22) ሰዎች በየቀኑ በሚያጋጥሟቸውና በተለመዱ ምሳሌዎች በመጠቀም በጣም የተወሳሰበውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርት በቀላሉ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል። አድማጮቻችን እየሰሙ ያሉት ነገር ምን እንደሆነ እንዲያስተውሉ የሚረዱ ቀስቃሽ ጥያቄዎችን መጠየቅ አለብን። መሪ ጥያቄዎች ወደ ትክክለኛው መደምደሚያ እንዲደርሱ ሊረዷቸው ይችላሉ።
7 ኢየሱስ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለሚፈልጉ ጊዜ ወስዶ ከበድ ያሉ ጉዳዮችን ያስረዳቸው ነበር። እንደ ደቀ መዛሙርቱ ያሉ እውነተኛ ፍላጎት ያላቸው ደግሞ ኢየሱስ ያስተማረው ነገር ጭብጡ ምን እንደሆነ ከእርሱ መረዳት ይችሉ ነበር። (ማቴ. 13:36) እኛም በተመሳሳይ በቅንነት ጥያቄ ሲቀርብልን መልሱን በመስጠት የምንረዳ መሆን አለብን። መልሱን ካላወቅነው ግን በጉዳዩ ላይ ከልዩ ልዩ ጽሑፎች ምርመር አድርገን መልሱን ይዘን በሌላ ቀን ልንመለስ እንችላለን።
8 ኢየሱስ ተጨባጭ ነገር በማሳየት ያስተምር ነበር። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ምንም እንኳ ጌታቸው ቢሆን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየው አርያነት ነው። (ዮሐ. 13:2–16) የትህትና መንፈስ የምናሳይ ከሆነ እያጠኑ ያሉት ሰዎች የተማሩትን ነገር በተግባር ለማዋል ይገፋፋሉ።
9 ኢየሱስ የሰዎችን ልብ እንዲሁም ለጽድቅ ያላቸውን ፍቅር በመቀስቀስ ያስተምር ነበር። የእኛም ፍላጎት የሰዎችን ልብ ለመንካት መሆን አለበት። ሰዎች በተፈጥሯቸው አንድን የበላይ አካል የማምለክና ከሌሎች ጋር በሰላምና በደስታ የመኖር ፍላጎት ስላላቸው ለዚህ የተፈጥሮ ባሕርይ ማራኪ የሆነ ነገር ማቅረብ አለብን።
10 በታኅሣሥ ወር ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ቀርቧል! የተባለውን መጽሐፍ በማበርከት ስለ ክርስቶስ የተማርናቸውን ነገሮች ለሌሎች ለማካፈል እንችላለን። የኢየሱስን የማስተማር ችሎታ መኮረጃችን እሱ ያስማረውን ትምህርት ቅን ለሆኑ ሰዎች በምንነግርበት ጊዜ ለመስማት እንዲገፋፉ ሊረዳቸው ይችላል።— ማቴ. 10:40