ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ የሆነው የግል ጥናት
1 በጣም የሚያሳስቡን የትኞቹ ነገሮች ናቸው? ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረትንና ይህንን ዝምድና ጠብቆ ማቆየት በጣም ሊያሳስበን ይገባል። እንደዚህ ዓይነቱን ቅርርብ ለማዳበር የግል ጥናት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ዛሬ አብዛኛውን ጊዜያችንን በጥናትና በማሰላሰል ለማሳለፍ የሚያስችል ሁኔታ ያለን እምብዛም ነን። ሆኖም የአምላክን ቃል ዘወትር ካላነበብን የዓለምን መንፈስና ሥጋዊ ፍላጎቶቹን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እስክናጣ ድረስ ልንዳከም እንችላለን።
2 ለቃሉ ጉጉት ማሳደር፦ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አምላክ ዓላማዎች በተማርንበት ወቅት የበለጠ ለማወቅ ጓጉተን እንደነበረ አያጠራጥርም። ከጊዜ በኋላ ግን ለመንፈሳዊ ምግብ ያለን ረሃብ እየቀነሰ መጥቶ ሊሆን ይችላል። ለመንፈሳዊ ምግብ ‘ጉጉት ማሳደር’ ያስፈልገን ይሆናል። (1 ጴጥ. 2:2 አዓት ) እንዲህ ዓይነቱን ጉጉት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
3 የሚወዱት ምግብ ሽታ የሚያስደስት ትዝታ ስለሚፈጥር የምግብ ፍላጎት ይቀሰቅሳል። አጫጭር የግል ጥናት ወቅቶችም በመንፈሳዊ ሁኔታ ተመሳሳይ ስሜት ሊፈጥሩብን ይችላሉ። ጣፋጭ የሆኑ ጥቂት መንፈሳዊ ቁራሾችን መቅመሳችን ጥልቅ እውነቶችን የማወቅ ፍላጎታችንን ሊቀሰቅስ ይችላል። እውቀት በማግኘት የምናገኘው ደስታ የአምላክን ቃል በጥልቅ እንድንቆፍር ያነሳሳናል።
4 ይበልጥ ውጤት የሚያስገኝልህን ልማድ አዳብር፦ አንዳንዶች ምሽቱን በሙሉ ለግል ጥናት ሲመድቡ ሌሎች ደግሞ ይበልጥ አጭር የሆኑና የሚዘወተሩ የጥናት ጊዜያትን ይመርጣሉ። ማለዳ ላይ በተሻለ መንገድ ሐሳብህን አሰባስበህ ማጥናት እንደምትችል ከተሰማህ ከቁርስ በፊት ጥቂት ለማጥናት ልትወስን ትችላለህ። ይበልጥ ንቁ የምትሆነው በምሽት ከሆነ ከመተኛትህ በፊት ለማጥናት ትመርጥ ይሆናል። በየትኛውም ጊዜ አጥና ዋናው ተፈላጊ ነገር አዘውታሪና ይበልጥ ውጤት የሚያስገኝልህን ልማድ የሙጥኝ ማለትህ ነው።
5 በግል ጥናታችን ረገድ የበለጠ እንድንሠራ ማበረታቻ ሲሰጠን ጊዜዬ በሙሉ በፕሮግራም የተጣበበ ነው ለማለት እንቸኩል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁላችንም ብንሆን ጊዜያችንን እንዴት እንደምናጠፋ ስንገመግም ሐቀኞች መሆን አለብን። በየዕለቱ ቴሌቪዥን በማየት ብዙ ሰዓት እናባክናለን? አንዳንድ የግል ፍላጎቶቻችንን ለመሠዋት ፈቃደኛ ነን? ከሐቁ ሳንሸሽ ጊዜያችንን እንዴት እንደምናጠፋ ስንመረምር የግል ጥናት በማድረግ ይበልጥ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ጊዜያት ልናገኝ እንችላለን።— ኤፌ. 5:15, 16
6 የአምላክን ቃል ማጥናት ያልተከፋፈለ ትኩረታችንን ይጠይቃል። እያጠኑ ሌላ ነገር ለመሥራት መሞከር ከጥናቱ የሚገኙትን ጥቅሞች ይቀንሳል። እያጠናን መብላት፣ ሬዲዮ ማዳመጥ ወይም ቴሌቪዥን ማየት የምንወድ ከሆነ በምንማረው ነገር ላይ መመሰጥ አንችልም። (1 ጢሞ. 4:15) ስለዚህ ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል።— የትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ገጽ 33–4ን ተመልከት።
7 በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በተግባር ላይ ማዋል በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ከይሖዋ መመሪያ የምናገኘው በዚህ መንገድ ነው። ወረቀቱ ላይ የሰፈረው እውነት ልብህን እንዲለውጠው አድርግ። ምንም ያህል አጭር ቢሆን የምታገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ለማንበብ፣ ለመከለስ ወይም ለማሰላስል ተጠቀምበት።— ዘዳ. 6:6–8፤ ቆላ. 1:9, 10