ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተመልሶ ማነጋገር አጣዳፊ ነው
1 “ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን። እነሆ፣ ይህን አላውቀውም ብትል፣ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን?” የሚሉት በምሳሌ 24:11, 12 ላይ ያሉት ቃላት የምናገለግልበትን አንዱን አንገብጋቢ ምክንያት ጠንከር አድርገው ይገልጹልናል። በአጭሩ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ይህንን ሐሳብ የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ እንዲህ በማለት ከሰጠው ተልዕኮ ጋር ማያያዝ እንችላለን:- “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” እነዚህን ቃላት በመታዘዝ ሰዎችን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማድረግ አለብን።
2 የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ሰዎች እንዲድኑ አይፈልግም። አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና ትክክለኛውን የእውነት እውቀት እንዲያገኙ ያለውን ፍቃድ ሰይጣን ለማደናቀፍ ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:3, 4 አዓት) በዚህም ምክንያት በስብከት ሥራችን ተስፋ እንድንቆርጥ ለማድረግ ይጥራል። ተስፋ ቆርጠን እንዳንሰብክ ማድረግ ካልቻለ ሌላ የተንኮል ዘዴ ይሸርባል፤ ይህም የተንኮል ዘዴው ያገኘናቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እንድንረሳ ማድረግ ነው። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ በማድረጉ ወሳኝ የአገልግሎት ዘርፍ ረገድ ግዴለሾች በመሆን በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ንቁዎች መሆን አለብን።
3 ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ብዙ አስፋፊዎች “ይህንን ሰው አልረሳውም። እንደማስታውሰው ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም” ብለው ራሳቸውን በማሞኘት ፍላጎት ያሳየውን ግለሰብ በማስታወሻ እንደማይዙ ተስተውሏል። ይህም አንዱ የሰይጣን ማታለያ ሊሆን ይችላል። እውነታዎቹ እንደሚያሳዩት አእምሯችን በብዙ አዳዲስ ሐሳቦች ሲያዝ በአእምሯችን ይዘናቸው የነበሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ብዙውን ጊዜ እንረሳቸዋለን፣ ሌላው ቢቀር ያነጋገርነውን ሰው በተመለከተ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችን እንዘነጋለን። ነገር ግን ይህ ግዴለሽነት በሌላ መንገድም ሊከሰት ይችላል። አንድ ወንድም ከአራት ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ በአገልግሎት ያገኛቸውን ሰዎች ዝርዝር የጻፈበት ማስታወሻ እንዳለውና እነዚህን ሰዎች በፍጹም ተመልሶ እንዳላነጋገራቸው ለአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ነግሮታል! ተመልሶ ለማነጋገር የነበረውን የመጀመሪያ ዕቅድ ወደ ፍጻሜ እንዳያደርስ አንድ የሆነ ነገር አግዶታል። የአምላክ ጠላት ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ችላ እንደተባሉ ሲመለከት አይደሰትምን?
4 እርግጥ ነው፣ ይህ ቸልተኝነት ሆን ተብሎ የተደረገ ላይሆን ይችላል። በግለሰብ ደረጃ በሚገባ የተደራጀን አለመሆን አንዳንድ ጊዜ ቸልተኝነት ሊያስከትል ይችላል። ቢሆንም ይህንን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ማሻሻል አንድንችል መጸለይ እንችላለን፤ ደግሞም መጸለይ አለብን። በተጨማሪም ተመላልሶ መጠየቅ የማድረግ ልምድ ማጣት ተመልሰን ከመሄድ እንድናመነታ ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን፣ የመጽሐፍ ጥናት መሪውንና ሌሎች ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎችን እንዲረዱን ልንጠይቃቸው እንችላለን። በሁሉም የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞችም ላይ ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች ይወጡልናል። አንዳንድ ጊዜ ዋናው ችግር ለነገሩ ክብደት አለመስጠት ሊሆን ይችላል። እንግዲያው የያዕቆብ 4:17 ቃላትን በማስታወስ ይቅርታ እንዲያደርግልንና ወደፊት የተሻለ ለማድረግ እንዲረዳን ይሖዋን መጠየቅ ያስፈልገናል።
5 የእውነትን ዘሮች ለማሳደግ ተመላልሶ መጠየቆች አስፈላጊ ናቸው። (1 ቆሮ. 3:6, 7) በመጀመሪያው ውይይት ወቅት የተዘራውን ዘር ዲያብሎስ ወዲያውኑ እንዳይወስደው ይከላከላሉ። (ማቴ. 13:19) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አላቸው። (ሥራ 15:36) እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን የሚያስችል እርዳታ ያገኘነው በዚህ መንገድ እንደሆነ ተግባራዊ የሆኑ ተሞክሮዎች ይጠቁማሉ።— ማቴ. 11:19 የ1980 ትርጉም
6 ስለዚህ ለይሖዋና መሰሎቻችን ለሆኑ ሰዎች ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት መንገድ እንደመሆኑ መጠን ተመላልሶ መጠየቅን በተመለከተ ቁም ነገረኞች እንሁን። በዚህ ረገድ ድክመት ካለን ወደ ይሖዋ እየጸለይን ድክመቱን ለማስወገድ እንጣር። ተመላልሶ መጠየቆችን ለማድረግ ጊዜ አመቻቹ። አስቀድማችሁ ተዘጋጁ። ተመላልሶ መጠየቆቹን በተመለከተ አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን በማስታወሻ ያዙ። ተመላልሶ መጠየቅን አክብዳችሁ ለመመልከት ስለሚረዳችሁ ተመላልሶ መጠየቆቻችሁን መዝግባችሁ ሪፖርት አድርጉ። ይሖዋ አትረፍርፎ ይባርከናል፤ የሰዎችን ሕይወት ከማትረፋችንም በላይ ይህ ነው የማይባል ደስታ እናገኛለን።— ሥራ 20:35