በትምህርት ቤት ልታሳየው የሚገባ ክርስቲያናዊ ጠባይ
1 ገና ትምህርት በመከታተል ላይ ያለህ ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ ንጹሕ አቋምህን ሳታጎድፍ ለመኖር ጠንካራ እምነት ያስፈልግሃል። ለመጥፎ ባልንጀርነትና እምነትህን ሊፈትኑ ለሚችሉ ሁኔታዎች የተጋለጥክ ነህ። “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ . . . እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” የሚለውን የጴጥሮስ ምክር በሥራ ላይ ማዋልህ በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥ. 2:12) ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም ድፍረት ማሳየትና ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልግሃል።
2 በትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ ስትሆን ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የጾታ ግንኙነት፣ እምነት ማጉደል፣ ጸያፍ ንግግር፣ ሲጃራና አደንዛዥ መድኃኒቶች በሚያመጡት የሚበክሉ ተጽዕኖዎች ጥቃት ይደርስብሃል። ያስመዘገብከውን ጥሩ ስም የሚያበላሹ ፈተናዎች በየዕለቱ ያጋጥሙሃል። እንደዚህ ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁመህ ለማለፍ ከፈለግህ ልክ እንደ አዋቂዎች ሁሉ ‘ለእምነት መጋደል’ አለብህ።— ይሁዳ 3፤ የሐምሌ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 23–26 ተመልከት።
3 በትምህርት ቤት ውስጥ ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶችና ዓለማዊ በዓላት ይከበራሉ። በትምህርት ቤትህ ውስጥ የትኞቹ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ በዓላት እንደሚከበሩ ታውቃለህን? አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ‘መልካም ጠባይህን የሚነቅፉ ሰዎች . . . እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ለመያዝ’ ትችላለህን?— 1 ጴጥ. 3:16
4 የትምህርት ቤት ስፖርቶች ወይም ማኅበራዊ መዝናኛዎች ባላቸው ማራኪነት ትፈተን ይሆናል። እነዚህ አስደሳች የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች እምነትህን ሊያላሉ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለመገንዘብ ንቁ መሆን አለብህ። አንዳችሁ በሌላው እምነት በመታነጽ ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ የሚያስችሉህን ጓደኞች መምረጥ አስፈላጊ ነው።— ሮሜ 1:12
5 በይሖዋ እርዳታ ልትጸና ትችላለህ፦ ሰይጣን ያለማቋረጥ እምነትህን እየፈተነው ነው። ጽናትን የሚጠይቁብህ ፈተናዎች ከባድ ሊሆኑ ቢችሉም ከሚያስገኟቸው ጥቅሞች አንጻር ሲታዩ ሁሉም ጊዜና ጉልበት ቢጠፋላቸው የሚቆጩ አይደሉም። (1 ጴጥ. 1:6, 7) በራስህ ጥረት ብቻ ልትጸና አትችልም፤ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ መመልከት አለብህ። ኢየሱስ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 26:41) ሥነ ሥርዓት መያዝና ራስን መግዛት እጅግ አስፈላጊ ናቸው።— 1 ቆሮ. 9:27
6 ለምታሳየው ጠባይ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ እንደሆንክ ሁልጊዜ አስታውስ። (መክብብ 11:9) ምንም እንኳ የምታደርገውን ነገር ሌሎች ባያዩትም ይሖዋ የሚያውቀው ከመሆኑም በላይ ለፍርድ ያቀርብሃል። (ዕብ. 4:13) እርሱን ለማስደሰት ያለህ ልባዊ ምኞት ‘መዳንህን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንድትፈጽም’ ሊገፋፋህ ይገባል። (ፊልጵ. 2:12) የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል። መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ በጣም ጥሩ በሆኑ ምክሮችና ልንኮርጃቸው በሚገቡ ግሩም ምሳሌዎች የተሞላ ነው።— ዕብ. 12:1–3
7 ወላጆች እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሚና ትጫወታላችሁ። ልጆቻችሁን መቆጣጠር፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ማወቅና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እርዳታ መስጠት ይፈለግባችኋል። ከልጆቻችሁ ጋር በጥሩ ሁኔታ ትግባባላችሁን? ስለ አምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች አድናቆት የተሞላበት እውቀት በውስጣቸው ተክላችሁባቸዋልን? ልጆቻችሁ ተጽዕኖ ወይም ፈተና ሲያጋጥማቸው ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ አላቸው ወይስ በቀላሉ እጃቸውን ይሰጣሉ? ከእኩዮቻቸው የተለየ አቋም መያዝ ያለባቸው መሆኑ ተስፋ ያስቆርጣቸዋልን? ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን እነርሱን የመርዳት ኃላፊነት አለባችሁ። (ዘዳ. 6:6, 7) እናንተ የበኩላችሁን ኃላፊነት በጥሩ ሁኔታ ከተወጣችሁ ለእምነት በሚደረገው ውጊያ አሸናፊዎች እንዲሆኑ ልትረዷቸው ትችላላችሁ።— ምሳሌ 22:6