ቲኦክራሲያዊ ዜናዎች
▪ ባሳለፍነው የአገልግሎት ዓመት 12 በመቶ ጭማሪና ግሩም የሆነ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ተገኝቷል። 72 ጉባኤዎችና ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ብዙ ቡድኖች አሉን። ሰባት የመንግሥት አዳራሾች የተመረቁ ሲሆን ሌሎች ጉባኤዎችም የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ዕቅድ አላቸው። በዚህ የአገልግሎት ዓመት 619 ሰዎች ተጠምቀዋል። በእያንዳንዱ ወር በአማካይ ከጠቅላላው አስፋፊዎች 24 በመቶው በአቅኚነት አገልግሎት አሳልፈዋል! ብዙ ጽሑፎችን ያበረከትን ቢሆንም ይህንን የአገልግሎት ዘርፍ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ እንደምናሰፋው ተስፋ እናደርጋለን። ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ካለን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ የምናደርገውን ተሳትፎ ጨምሮ በይሖዋ ሥራ ንቁና ትጉ እንሆናለን።
▪ “ደስተኛ አወዳሾች” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ ሲጠናቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በድምሩ ከ10,000 የሚበልጡ ሰዎች (አዲስ አበባ 9,075 አዋሳ ደግሞ 1,008) የተገኙ ሲሆን 316 ሰዎች ተጠምቀዋል። በምግብ አገልግሎት በኩል የተደረገው ቀለል ያለ ዝግጅት በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ በምሳ እረፍት ጊዜ እርስ በርስ በመጨዋወት ደስታ ለማግኘት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። ለመሰብሰቢያ ቦታው ክፍያ የወጣውን ወጪ ለመሸፈን ላደረጋችሁት ልግስና እናመሰግናችኋለን።