የጥያቄ ሣጥን
◼ “ወንድም” እና “እህት” በሚሉት ቃላት በተገቢው መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
“ወንድም” እና “እህት” በሚሉት ቃላት ቃል በቃል ስንጠቀም አንድ ዓይነት ወላጆች ያሏቸውን ሰዎች መጥቀሳችን ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ ተፈጥሯዊ ዝምድና ሞቅ ያለ ወዳጅነት ይፈጥራል፤ ወንድማማቾች ያላቸው ቅርርብ በማኅበራዊ፣ በአካባቢና በስሜታዊ ትስስሮች ይበልጥ ይጠናከራል።
ደቀ መዛሙርቱ ሲጸልዩ ይሖዋን “አባታችን” ብለው እንዲጠሩት ኢየሱስ አስተምሯቸዋል። በዚህ ቃል መጠቀማችን ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም የሚቀራረቡ አባላት ያሉት የአንድ ቤተሰብ ክፍል እንደሆንና ከወንድሞቻችን ጋር ውድ መንፈሳዊ ዝምድና እንዳለን ያሳያል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” በማለት ይህን ይበልጥ አጉልቶታል።— ማቴ. 6:9፤ 23:8
ከአምላክ ቤተሰብ ጋር ባለን የተቀራረበ መንፈሳዊ ትስስር እርስ በርሳችን በተለይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ “ወንድም” እና “እህት” ብለን እንጠራራለን። በእነዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ ስብሰባውን የሚመራው ወንድም የተጠመቁ ግለሰቦችን የጋራ የቤተሰብ ስም ከመጥራቱ በፊት “ወንድም” ወይም “እህት” በሚለው ቃል ይጠቀማል፤ በኢትዮጵያ ደግሞ “ወንድም” ወይም “እህት” ካለ በኋላ በግለሰቡ ስም ይጠቀማል።
አንድ ያልተጠመቀ ሰው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ቢፈልግስ? ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ሲሰበሰብ የቆየና ራሱን በመወሰን የይሖዋ ምሥክር ለመሆን አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ያለ ግለሰብ “ወንድም” ወይም “እህት” እከሌ ተብሎ ቢጠራ (ብትጠራ) ችግር የለውም። በተለይ ግለሰቡ ያልተጠመቀ አስፋፊ ከሆነ እንደዚህ ብሎ መጥራት ይቻላል።
በሌላ በኩል በስብሰባዎቻችን ላይ በቅርቡ መገኘት የጀመሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የአምላክ ቤተሰብ እንደሆኑ የሚያሳዩ እርምጃዎች አልወሰዱም። እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ቤተሰብ ጋር መንፈሳዊ ዝምድና ስላልመሠረቱ “ወንድም” ወይም “እህት” ተብለው አይጠሩም። ስለዚህ በስብሰባዎች ላይ በአካባቢው የተለመዱ መጠሪያዎችን ተጠቅመን እንጠራቸዋለን፤ ለምሳሌ ያህል “አቶ” እከሌ ብለን ልንጠራቸው እንችላለን።
በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ “ወንድም” ወይም “እህት” በሚሉት መጠሪያዎች መጠቀማችን የተጸውኦ ስሞች ከሚያመለክቱት የበለጠ ቅርርብና ውድ ዝምድና እንዳለን ያሳያል። በአንዱ አባት በይሖዋ አምላክ ሥር በሚገኝ ቤተሰብ ውስጥ ያለንን እጅግ የተባረከ ዝምድና ያስታውሰናል። በተጨማሪም እርስ በርስ ያለንን ጥልቅ ፍቅርና መዋደድ ያስታውሰናል።— ኤፌ. 2:19፤ 1 ጴጥ. 3:8