እንዳሁኑ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት ያገኘንበት ጊዜ የለም!
1 አብዛኞቹ ሰዎች “እንደ አሁኑ አልፎልኝ አያውቅም!” ለማለት የሚችሉበትን ቀን ይናፍቃሉ። እንዲህ ለማለት የሚችሉት ‘ለማረፍ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣትና ራሳቸውን ለማስደሰት’ የሚያስችሏቸው የተትረፈረፉ ቁሳዊ ነገሮች ሲያገኙ እንደሆነ ያስባሉ። (ሉቃስ 12:19) በሌላ በኩል በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሁሉ ነገር ተሟልቶልናል ማለት እንችላለን። (መዝ. 34:10) እንደዚህ ለማለት የሚያስደፍረን ምንድን ነው?
2 ምሳሌ 10:22 “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች” ይላል። ይህን መለኮታዊ ሞገስ ያገኘን ሰዎች አምላክ ‘ደስ እንዲለን ሁሉን አትረፍርፎ ይሰጠናል’ በማለት አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። (1 ጢሞ. 6:17) ይህም በምድር ላይ ካሉት ሁሉ የላቅን ሀብታሞች ያደርገናል!
3 ያገኘናቸውን በረከቶች መለስ ብለን ማሰብ፦ ብዙዎቻችን የተትረፈረፉ ቁሳዊ ነገሮች የሉንም። ሆኖም በየዕለቱ ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ከመጠን በላይ ስለማንጨነቅ ተባርከናል። ይሖዋ ምን ነገር እንደሚያስፈልገን ከማወቁም በተጨማሪ እነዚህን ነገሮች እንደሚያሟላልን ቃል ገብቶልናል። (ማቴ. 6:31-33) የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ያለን እምነት በዋጋ ሊተመን የማይችለውን የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል።
4 ሆኖም ያገኘናቸው መንፈሳዊ በረከቶች ከዚህ ይበልጣሉ። ሕይወታችን የተመካው ከይሖዋ በምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ ላይ ነው። (ማቴ. 4:4) እኛ እስከምንረካ ድረስ ስንበላና ስንጠጣ ከዓለማዊ ምንጮች መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎች እየተራቡ ነው። (ኢሳ. 65:13) ‘ታማኙ ባሪያ’ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከሚፈልቅበት የማይነጥፍ ምንጭ እንድንጠቀም አስችሎናል።— ማቴ. 24:45፤ ዮሐ. 17:3
5 ውድ የሆነው ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነታችን በመላው ምድር ከሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ከልብ በመነጨ ፍቅር አስተሳስሮናል። (ዮሐ. 13:35) ጉባኤያችን መጽናኛ የምናገኝበትና መንፈሳችን የሚታደስበት ሰላማዊ መሸሸጊያ ነው። ሽማግሌዎች በንቃት ይጠብቁናል፤ በተጨማሪም የተለያዩ ችግሮቻችንን እንድናሸንፍ ይረዱናል። (ዕብ. 13:17) ከወንድሞቻችን ጋር መቀራረባችን እርስ በርስ ለመበረታታት ከማስቻሉም በላይ ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል።— ሮሜ 1:11, 12
6 የተሰጠን ሥራም ቢሆን በረከት ነው። ብዙዎቹ ሰብዓዊ ሥራዎች አሰልቺና እርካታ የማይገኝባቸው ናቸው። ምሥራቹን መስበክ ግን ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ደስታ ያስገኛል። (ሥራ 20:35) የድካማችንን ፍሬ ማየት እንችላለን።— መክ. 2:24
7 ከሁሉም በላይ ደግሞ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስደናቂ ተስፋ አለን። (ሮሜ 12:12) ደስታና ሰላም አግኝተን ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ለዘላለም መኖር የምንችልበት ፍጹም የሆነና ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንጠባበቃለን! ይህ ተስፋ ዓለም ከሚያቀርብልን ማንኛውም ነገር የበለጠ ዋጋ ያለው ሀብት ነው።— 1 ጢሞ. 6:18, 19
8 አድናቆታችንን እንዴት ማሳየት እንችላለን? ይሖዋ ላደረገልን ነገር ውለታ መመለስ ፈጽሞ አንችልም። አድናቆታችንን የምናሳየው በሚከተሉት መንገዶች ብቻ ነው:- (1) ይገባናል ለማንለው ደግነቱ ይሖዋን በየዕለቱ ስናመሰግን (ኤፌ. 5:20)፣ (2) ታዛዥ በመሆን ፍቅራችንን ስናሳይ (1 ዮሐ. 5:3)፣ (3) ምሥራቹን በመስበክ ስሙን ስንቀድስ (መዝ. 83:18 አዓት) እና (4) ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ከሙሉ ልብ የመነጨ ትብብር በማድረግ ድጋፍ ስንሰጥ።— 1 ጢሞ. 3:15
9 በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ደስተኛ የምንሆንባቸው በቂ ምክንያቶች አሉን። (መዝ. 144:15 አዓት) ዝንባሌያችን፣ ጠባያችንና አገልግሎታችን ባለንበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ እያገኘን ያለነውን ደስታ የሚያንጸባርቅ ይሁን። እንደ አሁኑ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት ያገኘንበት ጊዜ የለም!