ተልዕኮ ተሰጥቶናል
1 ኢየሱስ ተከታዮቹን “አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ አዟቸዋል። (ማቴ. 28:19) በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 232 አገሮችና ደሴቶች ያሉ ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ አምላክ አወዳሾች ኢየሱስ ለሰጠው ትእዛዝ ፍጻሜ የሚሆኑ ሕያው ምሥክሮች ናቸው። ይሁን እንጂ እኛ በግላችን እንዴት ነን? እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልዕኮ በቁም ነገር እንይዘዋለን?
2 ሥነ ምግባራዊ ግዴታ፦ ተልዕኮ “እንዲሠራ የተሰጠን ትእዛዝ መፈጸም” ማለት ነው። እኛም እንድንሰብክ ክርስቶስ ትእዛዝ ሰጥቶናል። (ሥራ 10:42) ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን ማወጅ በእርሱ ላይ የተጣለ ኃላፊነት ወይም የሥነ ምግባር ግዴታ እንደሆነ ተገንዝቧል። (1 ቆሮ. 9:16) በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንዲት በመስጠም ላይ ያለች መርከብ ሠራተኛ ነህ እንበል። ካፒቴኑ ተጓዦችን እንድታስጠነቅቅና ሕይወት አድን ጀልባ ወዳለበት ቦታ እንድትመራቸው አዘዘህ። ትእዛዙን ችላ ብለህ ራስህን ብቻ ለማዳን ትጣደፋለህን? አታደርገውም! የሌሎቹ ሕይወት የተመካው በአንተ ላይ ነው። ሕይወታቸው በአደጋ ላይ ወድቋል! እነርሱን ለመርዳት የተሰጠህን ተልዕኮ የመፈጸም ሥነ ምግባራዊ ግዴታ አለብህ።
3 እኛም ማስጠንቀቂያ የማሰማት መለኮታዊ ተልዕኮ ተሰጥቶናል። ይሖዋ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ ያጠፋዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት በቋፍ ላይ ይገኛል! በሌሎች ሰዎች ላይ የተደቀነውን አደጋ ችላ ብሎ ማለፍና ራሳችንን ብቻ ለማዳን መጣደፍ ትክክል ነውን? በእርግጥ ትክክል አይደለም! የሌሎችን ሰዎች ሕይወት ለማዳን እርዳታ የመስጠት ሥነ ምግባራዊ ግዴታ አለብን።— 1 ጢሞ. 4:16
4 ልንከተላቸው የሚገቡ ታማኝ ምሳሌዎች፦ ነቢዩ ሕዝቅኤል ከሃዲ ለነበሩት እስራኤላውያን የማስጠንቀቂያ መልእክት የማሰማት ኃላፊነት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። የተሰጠውን ሥራ ባያከናውን ውጤቱ ምን እንደሚሆን ይሖዋ ጠበቅ አድርጎ አስጠንቅቆት ነበር። “እኔ ኃጢአተኛውን:- በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ አንተም ባታስጠነቅቀው . . . ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።” (ሕዝ. 3:18) ሕዝቅኤል ከባድ ተቃውሞ ቢደርስበትም እንኳ የተሰጠውን ተልዕኮ በታማኝነት ፈጽሟል። በመሆኑም የይሖዋ ፍርድ በጀመረበት ጊዜ ሊደሰት ችሏል።
5 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለመስበክ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ጽፏል። “እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ . . . የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና” በማለት ገልጿል። ጳውሎስ በሕዝብ ፊትና ከቤት ወደ ቤት ሰብኳል፤ ምክንያቱም እንዲህ ባያደርግ በአምላክ ፊት በደም ሊጠየቅ እንደሚችል ጠንቅቆ አውቋል።— ሥራ 20:20, 26, 27
6 የሕዝቅኤል ዓይነት ቅንዓት አለንን? እንደ ጳውሎስ ለመስበክ የሚገፋፋን ስሜት አለንን? የተሰጠን ተልዕኮ እነርሱ የተሰጣቸው ዓይነት ነው። ምንም እንኳ ሰዎች ግዴለሾች፣ ቸልተኞች ወይም ተቃዋሚዎች ቢሆኑም ሌሎችን እንድናስጠነቅቅ የተሰጠንን ኃላፊነት ለመፈጸም ሳናቋርጥ ወደፊት መግፋት አለብን። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ በመስጠት “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።” (ዘካ. 8:23) ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር እንዳንታክት ያድርገን። እንድንሰብክ ተልዕኮ ተሰጥቶናል!