የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ በኢትዮጵያ
1 በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን መስክ ስንመለከት፣ በይሖዋ ምድራዊ ድርጅት እየታየ ያለው ከፍተኛ ጭማሪ ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነው። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ በድምሩ 3,288 ጉባኤዎች ተጨምረዋል። ከዚህ ሁሉ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ማስፈለጋቸው ምንም አያስደንቅም።
2 ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጊዜያቸውንና ንብረታቸውን ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ በፈቃደኝነት በማቅረብ ለይሖዋ ድርጅት ያላቸውን ከፍተኛ ቅንዓትና ድጋፍ አሳይተዋል። የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች እነዚህን ፕሮጀክቶች በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ድካማቸውም ይደነቃል። መላው የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ዝግጅት የሚከናወነው በዓለም ሰፍኖ ከሚታየው መንፈስ ተቃራኒ በሆነው በክርስቲያናዊው የመስጠትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አማካኝነት ነው።—2 ጢሞ. 3:2, 4
3 ፈቃደኛ ሠራተኞች ለመልካም ሥራ ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው:- በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ ለመርዳት በፈቃደኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ ማኅበሩ አመስጋኝ ነው። በሁሉም ዓይነት የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ዘርፎች ለመሳተፍ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ማግኘቱ ከልብ የሚያስደስት ነው። ከጉባኤዎቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ሊያሳልፉት የሚችሉትን ጊዜ በመሠዋት ይህን የመሰለ የፈቃደኝነት፣ የልግስናና የመተባበር መንፈስ በፈቃደኛ ሠራተኞች በኩል መታየቱ ፕሮግራሙ ስኬታማ እንዲሆን አስችሏል። (መዝ. 110:3 NW፤ ቆላ. 3:23) ይህን የመሰለ ፍቅራዊ ምላሽ በማሳየታቸው ልናመሰግናቸው፣ ልናደንቃቸውና ሙሉ ድጋፍ ልንሰጣቸው የሚገባቸው ሰዎች ናቸው።—ሮሜ 12:10፤ ዕብ. 13:1
4 በቋሚነት የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎችን ለመርዳት ብቁ የሆኑ ሁሉ የመንግሥት አዳራሽ ፈቃደኛ ሠራተኛ መጠይቅ ቅጽ (S-82-AM) እንዲሞሉ ተጠይቀዋል። ጉባኤው የአመልካቹን ብቃቶችና ዝግጁነት በመጥቀስ ቅጹን ለሕንፃ ሥራ ኮሚቴው ይልከዋል። በፈቃደኛ ሠራተኛው ሁኔታ ላይ የቦታ መቀየር ወይም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ መሾምን የመሰሉ ለውጦች ከተከሰቱ፣ አዲስ ቅጽ ወዲያውኑ ተሞልቶ በጉባኤው ፀሐፊ በኩል መላክ ይኖርበታል። አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ ብቃቱን ካጓደለ፣ ሽማግሌዎቹ ወዲያውኑ በደብዳቤ ለሕንፃ ሥራ ኮሚቴው ማሳወቅ አለባቸው። ተጨማሪ ቅጾች ካስፈለጉ በወርሃዊው የጽሑፍ ማዘዣ ቅጽ መጠየቅ ይቻላል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹም ቢሆን ለዚህ ቅዱስ የአገልግሎት መስክ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን ለማወቅ ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት ጉባኤውን በጎበኘ ቁጥር የመንግሥት አዳራሽ ፈቃደኛ ሠራተኛ መጠይቆች ቀሪ ቅጂዎችን የያዘውን ፋይል ይመረምራል።
5 የግንባታ ወጪዎችን በተቻለ መጠን መቀነስ:- የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች ብቃት ባለው ሽማግሌ ተቆጣጣሪነት የግዢ ክፍል እንዲያደራጁ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ወንድሞች የሚያዋጣ ዋጋ ለማግኘት ሲሉ የገበያ ዋጋዎችን በሚገባ በማነጻጸር ግዥዎችን ያከናውናሉ። የግንባታው ገንዘብ በተቻለ መጠን ቁጠባ በተሞላበት መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ የአካባቢ ሕንፃ ሥራ ኮሚቴው ሁሉንም ወጪዎች ማጽደቅ አለበት። አዲስ የሚገነባም ሆነ የሚታደስ የመንግሥት አዳራሽ ፕሮጀክት በአዳራሹ ከሚሰበሰበው/ቡት ጉባኤ/ዎች ውጪ የፈቃደኛ ሠራተኞች እርዳታ ከሌሎች ጉባኤዎች ከተጨመረበት ምን ጊዜም ቢሆን የሕንፃ ሥራ ኮሚቴው ፕሮጀክቱን በበላይነት ይቆጣጠራል።
6 ምንም እንኳን በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የአብዛኛው የሰው ዘር ፍቅር የቀዘቀዘ ቢሆንም፣ የአምላክ ሕዝቦች አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ከዘርና ከብሔራዊ ድንበሮች አልፎ የሚሄድ መሆኑን በተጨባጭ ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። (ማቴ. 24:12) ሰማያዊ አባታችንን በመምሰል የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን በፈቃደኝነት በመደገፍ በኩል ይህን የመሰለውን ፍቅር ማሳየታችንን እንቀጥል። ይህን ማድረጋችን የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከትና ተቀባይነት ያስገኝልናል።—ሚል. 3:10፤ ዕብ. 6:10