ልጆች ሆይ፣ በእናንተ ደስ ይለናል!
1 ልጆች ሆይ፣ በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እናንተም እንድትካተቱ ይሖዋ የሰጠው መመሪያ እንዳለ ታውቃላችሁን? (ዘዳ. 31:12፤ መዝ. 127:3) ከእናንተ ጋር ሆኖ ይሖዋን ማምለክ እጅግ ያስደስታል! በስብሰባዎች ላይ ፀጥ ብላችሁ ተቀምጣችሁ በደንብ ስታዳምጡ ስናይ በጣም ደስ ይለናል። በተለይ ደግሞ በራሳችሁ አባባል መልስ ለመስጠት ስትሞክሩ መስማት ያስደስተናል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ተሰጥቷችሁ ስታቀርቡ፣ በፍላጎት ከእኛ ጋር በመስክ አገልግሎት ስትካፈሉ እንዲሁም ለትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁና አስተማሪዎቻችሁ በድፍረት እንደምትመሰክሩ ስንሰማ የጉባኤው አባሎች ሁላችን እንደሰታለን።—መዝ. 148:12, 13
2 መልካም ጠባያችሁን፣ ሥርዓታማ አለባበሳችሁን፣ ንፁህ ሥነ ምግባራችሁንና ለአዋቂዎች ያላችሁን አክብሮት ስንመለከት እንደምንኮራባችሁ እንድታውቁ እንፈልጋለን። በተለይ ደግሞ ቲኦክራሲያዊ ግቦችን በማውጣት ‘ታላቁ ፈጣሪያችሁን እንደምታስታውሱ’ ስታሳዩ ደስታችን ወደር የለውም።—መክ. 12:1 NW፤ መዝ. 110:3 NW
3 ግባችሁን ንገሩን፦ አንድ የስምንት ዓመት ልጅ ለአንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች እንዲህ በማለት ነግሮታል:- ‘በመጀመሪያ መጠመቅ እፈልጋለሁ፤ ከዚያም በድምፅ ክፍልና የድምፅ ማጉያ በማዞር፣ አስተናጋጅ በመሆን፣ በጽሑፍ ክፍል በመሥራት እንዲሁም በመጽሐፍ ጥናትና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት አንባቢ በመሆን በጉባኤው ውስጥ ማገልገል እፈልጋለሁ። ከዚያም የጉባኤ አገልጋይ ቀጥሎም የጉባኤ ሽማግሌ መሆን እፈልጋለሁ። አቅኚ በመሆን የአቅኚዎችን ኮርስ መካፈል እፈልጋለሁ። ቀጥሎም ቤቴል መግባት፣ የወረዳ የበላይ ተመልካች ወይም የአውራጃ የበላይ ተመልካች መሆን እፈልጋለሁ።’ አምላክን የማገልገልን መብት በተመለከተ ያለው አድናቆት ምንኛ ከፍተኛ ነው!
4 በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ አድጋችሁ ግባችሁ ላይ ስትደርሱ ማየት በጣም ያስደስተናል። (ከሉቃስ 2:52 ጋር አወዳድር።) ከእናንተ መካከል በሺህ የሚቆጠሩት በየዓመቱ ያልተጠመቁ አስፋፊዎችና ለይሖዋ ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮች በመሆን ለጥምቀት የሚበቁ ይሆናሉ። ከዚያም ረዳት አቅኚ አልፎ ተርፎም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆናችሁ ስናይ ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል። ልጆች በእርግጥም በእናንተ ደስ ይለናል፤ እናንተን ስለ ሰጠን የሰማዩ አባታችንን ከልብ እናመሰግናለን። ይሖዋ አብዝቶ ይባርካችሁ!—ምሳሌ 23:24, 25