‘የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው’
1 በሉቃስ ምዕራፍ 10 ላይ ኢየሱስ ወዳጆቹን ለመጠየቅ ወደ ቢታንያ መሄዱን የሚገልጽ ታሪክ እናነባለን። ማርያም በዚህ አጋጣሚ ተጠቅማ የተቻላትን ያህል ከኢየሱስ ትምህርት ለማግኘት ከመጣርዋም በላይ በሚያንጽ ጭውውት ላይ ትኩረት አድርጋለች። ሆኖም እህቷ ማርታ የተዋጣላት አስተናጋጅ ለመሆን በመጣር በሥራ ተጠምዳ ነበር። ኢየሱስ አስፈላጊው ነገር መንፈሳዊ ትምህርት የሚገኝበት ክርስቲያናዊ ጭውውት ማድረግ መሆኑን ለማርታ አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ነግሯታል። ኢየሱስ “የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው” አላት።—ሉቃስ 10:42
2 እንግዳ ተቀባይነትን አስመልክቶ በአገራችን ካለው ባሕላዊ ልማድ በመነሳት ብዙዎች ወንድሞቻቸውን ለመጠየቅ ሲሄዱ ባዶ እጃቸውን መሄድ እንደሌለባቸው ወይም ሌሎችን በእንግድነት ለመቀበል ትልቅ ግብዣ ማድረግ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። የኢኮኖሚ ችግር ባለበት በአሁኑ ወቅት እንዲህ ለማድረግ አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ጥቂቶች ናቸው። ይህም በመሆኑ ወንድሞቻቸውን ከመጠየቅ ወይም የእምነት ጓደኞቻቸውን ከመጋበዝ በመቆጠብ ብዙውን ጊዜ ጥሩ አጋጣሚዎች ያመልጧቸው ይሆናል። የኢየሱስን ፈለግ ስንከተል “የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው” በማለት ለማርታ የተናገራቸውን ቃላት ማስታወሳችን ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ተገቢም ነው።—1 ጴጥ. 2:21
3 እጅግ አስፈላጊና ገንቢ ለሆነ ጭውውት በር የሚከፍቱ በርካታ ጥሩ አጋጣሚዎች አሉ። በቡድን መልክ በአንድ አካባቢ ስታገለግሉ ቆይታችሁ አገልግሎት ከጨረሳችሁ በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች አንድ ላይ በመሆን አንድ ወይም ሁለት የሚያንጹ ተሞክሮዎችን ለምን አትለዋወጡም? ምናልባትም የሚያስፈልገው “አንድ ነገር” ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ስጦታ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ቆሎ፣ ኦቾሎኒ ወይም የሚጠጣ ውኃ ማቅረብ ትችላላችሁ። የአንድ መጽሐፍ ጥናት ቡድን አባላት አልፎ አልፎ ከስብሰባው በኋላ እዚያው ጥቂት ደቂቃዎች በመቆየት ከጽሑፎቻችን ያነበቧቸውን ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦች በማንሳት መጫወት ይችላሉ። ምናልባትም ቡድኑ ውስጥ ካሉት አንዳንዶች ገንዘብ አዋጥተው ጥቂት ብርቱካን በመግዛት ለሁሉም እንዲዳረስ ቆራርጦ ማቅረብ ይቻላል። አልፎ አልፎ ጥቂት ወንድሞችንና እህቶችን ሻይ ወይ ቡና በመጋበዝ አንዳንድ ገንቢ ጭውውቶች ማድረግም ይቻላል። ወይም አንድ ቦታ ከቆየን በኋላ እግረ መንገዳችንን በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ወንድም ቤት ጎራ ብለን ጥቂት ደቂቃዎች ማሳለፍ እንችላለን፤ ይዘን የምንሄደው ነገር አንድ ጥሩ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ተራ ነገሮች ቢሆኑም እርስ በርስ ያቀራርቡናል። ይህ ደግሞ ሰይጣንና እሱ ያቋቋመው ሥርዓት ጥቃት ለሚሰነዝሩበት ለመላው የወንድማማች ማኅበር እጅግ አስፈላጊ ነው።