ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች—ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች
1 በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል ከባድ ኃላፊነት ነው። (ሥራ 20:28፤ 1 ጢሞ. 3:1) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለእኛ ሲሉ የሚያከናውኑትን ጠቃሚ ሥራ መገንዘብ እንችል ዘንድ የሽማግሌዎችን የተለያዩ ተግባራት ከሚዘረዝሩት ተከታታይ ክፍሎች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነው።
2 ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ላልተወሰነ ጊዜ በዚሁ ቦታ እንዲያገለግል በማኅበሩ ይሾማል። የሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ የተቀናጀ አሠራር ሽማግሌዎች የተሰጣቸውን የሥራ ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ ይረዳቸዋል። (አገልግሎታችን ገጽ 42) የሚያከናውነው ተግባር ምን ምን ነገሮችን ያካትታል?
3 ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ወደ ጉባኤ የሚላኩትን ደብዳቤዎች ይቀበላል፤ ከዚያም የቀረውን ነገር እንዲያደርግ ወዲያው ለጸሐፊው ይሰጠዋል። የሽማግሌዎች ስብሰባ ከመደረጉ በፊት ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ውይይት ሊደረግባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ከሽማግሌዎች ሐሳብ ያሰባስብና አጀንዳ ያጠናቅራል። በተጨማሪም በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ሊቀመንበር ሆኖ ያገለግላል። ውሳኔዎች በሚተላለፉበት ጊዜ እያንዳንዱ ውሳኔ በትክክል መደረጉን ያረጋግጣል። የአገልግሎት ስብሰባ ዝግጅቶችንና ለሕዝብ ንግግሮች የሚወጡ ፕሮግራሞችን በበላይነት ይከታተላል። ለጉባኤ የሚነበቡ ማስታወቂያዎችን በሙሉ ያጸድቃል፣ የተለመዱ የጉባኤ ወጪዎች እንዲከፈሉ ያደርጋል እንዲሁም በየሦስት ወሩ የሚደረገው የጉባኤ የሒሳብ ምርመራ መደረጉን ያረጋግጣል።
4 ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ሊቀመንበር ሆኖ የጉባኤውን የአገልግሎት ኮሚቴ ሥራ ያስተባብራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ ወይም አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመጠመቅ በሚፈልግበት ጊዜ ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩት ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ዝግጅት ያደርጋል። በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ሳምንት ጉባኤው ሙሉ ጥቅም ያገኝ ዘንድ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ለጉብኝቱ ዝግጅት በማድረግ በኩል ቀዳሚ ሆኖ ይሠራል።
5 ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች የተለያዩ ብዙ ተግባሮችን ያከናውናል። ትሕትና በተሞላበት መንፈስ ኃላፊነቱን “በትጋት” በሚወጣበት ጊዜ እኛ ደግሞ ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበር የበኩላችንን ልናበረክት እንችላለን። (ሮሜ 12:8) ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩን ‘የምንታዘዝ’ እና ‘የምንገዛ’ ከሆነ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ሥራቸውን ሊያከናውኑ ይችላሉ።—ዕብ. 13:17