የይሖዋን የሕይወት መንገድ ለመከተል ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ
1 “የአምላክ የሕይወት መንገድ” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ አንዱ ጉልህ ገጽታ በመደምደሚያው ንግግር ላይ የተላለፈው የአቋም መግለጫ ነበር። የአቋም መግለጫው ሲጀምር “እኛ . . . የአምላክ መንገድ ከሁሉ የላቀ የሕይወት መንገድ እንደሆነ በሙሉ ልብ እንቀበላለን” ይል ነበር። “አዎ!” ብለን የተስማማንበትን የአቋም መግለጫ አንዳንድ ጎላ ያሉ ነጥቦች መለስ ብላችሁ አስታውሱ።
2 የዓለም ዕድፍ ሳይነካን በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሆነን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ መስጠታችንን እንቀጥላለን። የእርሱን ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያችን አድርገን በመጠቀም ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ፈቀቅ ሳንል በመመላለስ የአምላክ መንገድ ዓለም ከሚከተለው መንገድ እጅግ የላቀ መሆኑን እናረጋግጣለን።
3 በጥቅሉ ሲታይ ዓለም ለአምላክ የሕይወት መንገድ ደንታ ቢስ ሆኗል፤ ከዚህም የተነሣ መጥፎ ውጤቶችን እያጨደ ነው። (ኤር. 10:23) በመሆኑም “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” ብሎ ከሚነግረን ከታላቁ አስተማሪያችን ከይሖዋ መማራችንን መቀጠል አለብን። (ኢሳ. 30:21) በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሰፍሮ የሚገኘው የይሖዋ የሕይወት መንገድ በየትኛውም ዘርፍ አቻ የለውም። ይህን መንገድ መከተል እንድንችል ይሖዋ ከሚሰጠን ትምህርት የተሟላ ጥቅም ማግኘታችን አስፈላጊ ነው።
4 ይሖዋ ያቋቋመው የላቀ የትምህርት መርሐ ግብር፦ ይሖዋ ትክክለኛውን የሕይወት ዓላማና ሕይወታችንን እንዴት በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት እንደምንችል ያስተምረናል። በአስተሳሰብ፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ሕይወታችን የላቀ ደረጃ እንዲይዝ መሻሻል የምንችልበትን መንገድ ያስተምረናል። ከወንድሞቻችን፣ ከቤተሰቦቻችን እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር በሰላም መኖር የምንችልበትን መንገድ ያስተምረናል። ይህን የሚያደርገው ባዘጋጀው የመማሪያ መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ እና በድርጅቱ አማካኝነት ነው።
5 በዚህ ረገድ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። ዘወትር በአምስቱም ስብሰባዎች ላይ በተገኘንና በተሳተፍን መጠን ለምሥራቹ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለገብ ሥልጠና ከማግኘታችንም በተጨማሪ ክርስቲያናዊ አኗኗርን በሚመለከት ሚዛናዊ ትምህርት እናገኛለን። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ታላቁ አስተማሪያችን በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች አማካኝነትም ተጨማሪ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ይሰጠናል። ግባችን ጤንነታችንና ሁኔታችን እስከፈቀደልን ድረስ የትኛውም ስብሰባ ወይም የስብሰባ ክፍል ፈጽሞ እንዳያመልጠን ማድረግ ሊሆን ይገባል።
6 ይሖዋ እንዲወደስና ራሳችንም ዘላለማዊ ጥቅም እንድናገኝ ስንል ከፊታችን ባሉት ጊዜያት የአምላክን የሕይወት መንገድ ያለማወላወል መከታተላችንን እንቀጥል!—ኢሳ. 48:17