1 አዎን፣ ሰምተነዋል! ይሖዋ ለሕዝቦቹ ጥቅም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ነገሮችን ደጋግሞ ተናግሯል። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የተለያዩ ገጽታዎች የሰጣቸውን ትምህርቶች ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ተናግሯቸዋል። ሐዋርያቱ በእውነት ላይ ጽኑ መሠረት ለነበራቸው ሰዎች መንፈሳዊ ጉዳዮችን ደጋግመው ነግረዋቸዋል።—ሮሜ 15:15፤ 2 ጴጥ. 1:12, 13፤ 3:1, 2
2 በጊዜያችን የይሖዋ ድርጅት ከፍተኛ ቁም ነገር ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡ ዝግጅት አድርጓል። አንዳንድ ጽሑፎች በተደጋጋሚ ተጠንተዋል። አዎን፣ ከዚህ ቀደም የሰማናቸውን ነገሮች እንደገና መስማታችን ጠቃሚ ነው!
3 መደጋገም ትልቅ ድርሻ አለው፦ የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ጥልቅ ማስተዋል እንዲኖረን፣ የአመለካከት አድማሳችን እንዲሰፋ እንዲሁም በመንፈሳዊ ሕይወት ለመቀጠል ያደረግነው ውሳኔ እንዲጠናከር ያደርጋሉ። (መዝ. 119:129) የአምላክን የአቋም ደረጃዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መከለስ ራስን በመስተዋት የመመልከት ያህል ነው። እንዲህ ማድረጋችን ራሳችንን እንድንመረምርና ‘ሰምቶ የመርሳት’ አዝማሚያን እንድንዋጋ ይረዳናል።—ያዕ. 1:22-25
4 ደጋግመን ስለ እውነት ማሰባችንን ካልቀጠልን ሌሎች ነገሮች በልባችን ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ። አምላክ የሚሰጠን ማሳሰቢያዎች የሰይጣን ዓለም የሚያደርስብንን በካይ ተጽእኖዎች መቋቋም እንድንችል ያጠናክሩናል። (መዝ. 119:2, 3, 99, 133፤ ፊልጵ. 3:1) የአምላክን ዓላማዎች መፈጸም በተመለከተ ዘወትር የሚሰጡን ማሳሰቢያዎች “ትጉ” እንድንሆን ያነሳሱናል። (ማርቆስ 13:32-37) ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች መደጋገማቸው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚያመራው ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—መዝ. 119:144
5 በግል ጥቅም ማግኘት የምንችልበት መንገድ፦ ‘ልባችንን አምላክ ወደሚሰጠን ማሳሰቢያ ማዘንበል’ አለብን። (መዝ. 119:36) በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንድ የምናውቀው ርዕስ የሚጠና ከሆነ አስቀድሞ መዘጋጀት፣ የተጠቀሱትን ጥቅሶች እያወጡ ማንበብና ትምህርቱን እንዴት በሥራ ማዋል እንደምንችል ማሰብ አለብን። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚቀርበው የጽሑፍ ክለሳ አስፈላጊ እንዳልሆነ በማሰብ ከመዘጋጀት ወደኋላ ማለት የለብንም። (ሉቃስ 8:18) ብዙውን ጊዜ በስብሰባዎቻችን ላይ መሠረታዊ የሆኑ እውነቶች በድጋሚ መቅረባቸው ለትምህርቱ የምንሰጠውን ትኩረት ሊቀንስብን አይገባም።—ዕብ. 5:11
6 መዝሙራዊው “እንደ ብልጥግና [“ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ነገሮች፣” NW] ሁሉ በምስክርህ [“በማሳሰቢያህ፣” NW] መንገድ ደስ አለኝ” ሲል የነበረው ዓይነት ዝንባሌ ይኑረን። (መዝሙር 119:14) አዎን፣ እነዚህን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ከዚህ በፊት ሰምተናቸዋል፤ በድጋሚ እንደምንሰማቸውም ግልፅ ነው። ለምን? ይሖዋ እነዚህን ነገሮች መስማት እንደሚያስፈልገን ስለሚያውቅ ነው!