ክርስቶስ ላሳየው ፍቅር ምላሽ እየሰጣችሁ ነውን?
1 ሐዋርያው ዮሐንስ ጌታው ያሳለፈውን ሕይወት መለስ ብሎ በመመልከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።” (ዮሐ. 13:1) በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ስለ ክርስቶስ ታላቅ የፍቅር መግለጫ እናስባለን። በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን፣ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈልና እንደ ኢየሱስ ‘እስከ መጨረሻው በመጽናት’ እርሱ ላሳየን ፍቅር ምላሽ መስጠት እንችላለን።—ማቴ. 24:13፤ 28:19, 20፤ ዮሐ. 3:16
2 ክርስቶስ ላሳየን ፍቅር ምላሽ መስጠት:- ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ሳምንት ብዙ ነገር አከናውኗል። (ማቴ. 21:23፤ 23:1፤ 24:3) እኛም የክርስቶስን ፈለግ በመከተል በይሖዋ አገልግሎት ‘እንድንጋደል’ የሚገፋፋን ፍቅር ነው። (ሉቃስ 13:24) በአገልግሎቱ የምታሳልፉትን ሰዓት ከፍ በማድረግ በሚያዝያ ወር ተጨማሪ ምሥክርነት ለመስጠት የተደረጉትን ዝግጅቶች ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ?
3 በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ሚያዝያ 19 ረቡዕ ዕለት ምሽት ነው። ከፍተኛ ትርጉም ባለው በዚህ በዓል ላይ ምን ያህል ሰዎች ይገኙ ይሆን? ይህ በአብዛኛው የተመካው በእኛ ላይ ነው። በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ያሰባችኋቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር አውጥታችኋል? እነዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ ወይም ሌሎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች፣ ዘመዶቻችሁ፣ በሥራ ምክንያት የምታገኟቸው ሰዎች ወይም አብረዋችሁ የሚማሩ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ልባዊ የሆነ ግብዣ አቅርባችሁላቸዋል? የመታሰቢያው በዓል ከመድረሱ ከጥቂት ቀናት በፊትስ ደግማችሁ ልታስታውሷቸው አቅዳችኋል? ምናልባት በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ለመምጣት የእናንተ እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆን? ሽማግሌዎችም አገልግሎት ያቆሙትን በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ይጋብዟቸዋል። የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው በሳምንቱ መጨረሻ ሳይሆን በሥራ ቀናት ባለው ምሽት ላይ መሆኑ እያንዳንዱ ሰው በበዓሉ ላይ የመገኘቱን አስፈላጊነት አይቀንሰውም።
4 ተዘጋጅታችሁ ኑ:- በመታሰቢያው በዓል ላይ ስንገኝ በጥሩ ሁኔታ መዘጋጀታችንና ተገቢ አመለካከት መያዛችን በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ መሰል ክርስቲያኖች ለበዓሉ ተገቢውን አክብሮት ማሳየታቸውን እንዳይዘነጉ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 11:20-26) እናንተም በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ወቅት ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 13 እስከ ምዕራፍ 17 ድረስ ያለውን ካነበባችሁ በኋላ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለእርሱ ምን ትርጉም እንዳለው እንዲናገር ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ለመታሰቢያው በዓል ሳምንት የተመደበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ኘሮግራም ተከታትላችሁ ማንበብን አትርሱ!
5 ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ ፍቅራችንን የምናሳይበት አጋጣሚ ሚያዝያ 19 ብቻ አይሆንም። ለእሱ ያለንን ፍቅር ለዘላለም ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል! በዚህ ዓመት የሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ይህንን ውሳኔያችንን እንድናጠናክር ይረዳናል።