ከምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ደስታ ማግኘት
1 መጽሐፍ ቅዱስ 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት ሰፊ የስብከት ዘመቻ ካካሄዱ በኋላ ስላከናወኑት አገልግሎት ለኢየሱስ በነገሩት ጊዜ የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጽ ‘በደስታ ተመለሱ’ ይላል። የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው ውስጣዊ ደስታ ተሰምቷቸዋል። (ሉቃስ 10:17) እናንተስ ከምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ይህን የመሰለ ደስታ እንድታገኙ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?
2 አዎንታዊ አመለካከት:- ይሖዋ ሰዎችን ከእርሱ ታላቅ ዓላማ ጋር የማስተዋወቅ ልዩ መብት ሰጥቶአችኋል። በስብከታችሁ አማካኝነት አንድን ሰው ከዚህ ዓለም ወራዳ ድርጊቶችና ከሐሰት ሃይማኖት ማነቆ እንዲላቀቅ መርዳት ትችሉ ይሆናል። ዛሬ በዓለም ላይ የጠፋው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ስለሚሰፍንበት ጊዜ የሚገልጸውን ተስፋ ለሰዎች ማካፈል ትችላላችሁ። የእውነትን ዘር ተቀባይ በሆነ ልብ ውስጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ስትዘሩ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚደሰት ገምቱ። በሙሉ ልባችሁ በአገልግሎቱ ስትካፈሉ የአምላክ መንፈስ በውስጣችሁ የደስታን ፍሬ እንዲያፈራ በመጸለይ በኩል አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ።
3 ተግባራዊ ሥልጠና:- ኢየሱስ ለ70ዎቹ ደቀ መዛሙርት መመሪያ በመስጠት ያሳለፈው ጊዜ በዘመናችን ከሚካሄደው የአገልግሎት ስብሰባ ጋር ተመሳሳይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲችሉ ሥልጠና ሰጥቶአቸዋል። (ሉቃስ 10:1-16) ዛሬም የአገልግሎት ስብሰባ ሰዎችን ቀርባችሁ ለማነጋገር፣ ውይይት ለማስጀመር፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማግኘትና ለመምራት የምትችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች በተመለከተ ሥልጠና ይሰጣችኋል። ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታችሁ ከተከታተላችሁና የስብከት ችሎታችሁን ካሻሻላችሁ ይሰማችሁ የነበረው የመረበሽ ወይም ብቁ አይደለሁም የሚለው ስሜት ቀስ በቀስ እየቀነሰ ይሄድና በራስ በመተማመንና በደስታ ስሜት ይተካል።
4 በወደፊቱ ጊዜ ላይ አትኩሩ:- ኢየሱስ በጽናት የተቋቋማቸው መከራዎች ቢኖሩበትም ለአምላክ ከሚያቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ደስታ አግኝቶአል። ለምን? ዓይኑን የተከለው ከፊቱ ይጠብቁት በነበሩት በረከቶችና ልዩ መብቶች ላይ ስለነበር ነው። (ዕብ. 12:2) እናንተም አእምሮአችሁና ልባችሁ በይሖዋ ስምና በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በሚገኙት በረከቶች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ተመሳሳይ ውጤት ማግኘት ትችላላችሁ። ይህም አገልግሎታችሁ የበለጠ ትርጉም ያለውና ተጨማሪ ደስታ የምታገኙበት እንዲሆን ያደርግላችኋል።
5 ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ ዛሬ ልናገኘው ከምንችለው መብት ሁሉ የላቀ ልዩ መብት ነው። በመሆኑም “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ” ለማለት ያብቃችሁ።—መዝ. 40:8