የመንግሥት አዳራሻችሁን በመንከባከብ ረገድ የአንተ ድርሻ ምንድን ነው?
1 በደረቅ አካባቢ እንደሚገኝ የበረሃ ገነት በየስፍራው የሚገኙ የመንግሥት አዳራሾችም መንፈሳዊ እረፍትና ማነቃቂያ የሚገኝባቸው ቦታዎች ናቸው። የተለያዩ ሰዎች ስለ ይሖዋ ለመማር ወደዚህ ሕንፃ ይመጣሉ። እነዚህ ሰዎች የመንግሥት አዳራሹን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ አምልኮ የተወሰነ “ቤት” እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። አንተስ እንደዚህ ትመለከተዋለህ? በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ እዚያ ከሚመጡ ወንድሞችና እህቶች ጋር ለመጫወትና በውስጡ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ ትጓጓለህ?
2 የመንግሥት አዳራሹ በእያንዳንዱ ሳምንት ብዙ ጊዜ ለስብሰባ ስለሚያገለግል ጽዳትና ጥገና እንደሚያስፈልገው ምንም አያጠያይቅም። የመንግሥት አዳራሹን ንጹሕና ሥርዓታማ አድርጎ በመያዝ ረገድ ድጋፍ የመስጠት መብትህን በአድናቆት ትመለከተዋለህ? የመንግሥት አዳራሹ አገልግሎት የሚሰጥበትና አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ታይቶ በሚወጣ ቋሚ ፕሮግራም መሠረት መጽዳት ይገባዋል። ልጆችን ጨምሮ ሁሉም በማጽዳቱ ሥራ መካፈል ይችላሉ። ይህም ሁሉም የመንግሥት አዳራሹን የመንከባከቡን ኃላፊነት እንዲገነዘቡና ይበልጥ እንዲያደንቁ ይረዳል። ንጹሕና ሥርዓታማ በሆነ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብም ሆነ ሌሎችን በዚያ እንዲገኙ መጋበዝ ምንኛ አስደሳች ነው!—1 ቆሮ. 14:40
3 ብዙውን ጊዜ የጽዳት ፕሮግራም የሚወጣው የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖችን በየተራ በመመደብ ነው። በዚህ መንገድ ሁሉም ለአዳራሹ እንክብካቤ የማድረግ ድርሻ ስለሚኖራቸው ኃላፊነቱ በጥቂቶች ላይ ብቻ አይወድቅም። ጽዳቱ ምን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት የያዘውን ዝርዝር በሠሌዳው ላይ መለጠፍ ወይም በጽዳቱ ላይ ለሚገኙ ወንድሞች መስጠት ይቻላል። ጽዳቱ መስኮቶችን ማጽዳት፣ አቧራውን በጨርቅ ማንሳት፣ መጸዳጃ ቤቱን ማጽዳትና ወለሉን አልፎ አልፎ መወልወል እንዲሁም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እንጨት ነክ የሆኑ ነገሮችን ሰም መቀባት ሊያካትት ይችላል። የጽዳት መሣሪያዎች እንዲሁም ሰም ከማለቃቸው በፊት መገዛት አለባቸው። የመንግሥት አዳራሹን እንክብካቤ የሚከታተል፣ ፕሮግራም የሚያወጣ፣ የጽዳት መሣሪያዎች እንዲገዙ ጥያቄ የሚያቀርብና እድሳት ማስፈለጉን የሚከታተል አንድ የጉባኤ አገልጋይ መመደብ ይቻላል።
4 የመንግሥት አዳራሹ አጠቃላይ ገጽታ ክትትል ሊደረግለት ይገባል። ቀለሙ መታደስ የሚያስፈልገው ከሆነ በጣም ደማቅ ቀለም መጠቀም አያስፈልግም። ጥገና ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል። ሹል ነገሮች ወይም በደንብ ያልተመቱ ምስማሮች በቀላሉ ልብስ ሊቀድዱ ስለሚችሉ በቸልታ ማለፍ አይገባም። ግቢው ወይም የመኪና ማቆሚያ ስፍራው ትኩረት ያሻው ይሆን? ግቢው ውስጥ ሣር፣ አበባ ወይም የሚከረከም ጥድ ካለ በየጊዜው ማጨድና መከርከም አስፈላጊ ነው። በዓመት ሁለቴ ወይም ሦስቴ ብቅ እያለ ሣሩን የሚያጭድ ሰው መቅጠር ብቻ በቂ አይደለም። እንዲህ ማድረጉ ግቢው ለዓይን ማራኪ ሳይሆን ብዙ ወራት እንዲያልፉ ያደርጋል። እንዲሁም ለአምልኮ ከምንጠቀምበት አዳራሽ ፊት ለፊት ምንም ዓይነት ሰብል መዝራት አይገባም። ግቢው ውስጥ የመንግሥት አዳራሹን የሚጠብቅ ሰው የሚኖር ከሆነ የግቢውን ውበት የሚቀንስ ነገር በየቦታው መታየት አይኖርበትም። ጉባኤው ከፍተኛ ወጪ ሳያወጣ ውስጡን ይበልጥ ማራኪ ማድረግ የሚቻልባቸው መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ውስጡን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ በጣም ውድ ያልሆኑ ጥቃቅን ነገሮችን ማድረግ ይቻላል። ንጹሕ፣ ዕቃዎቹ በሥርዓት የተቀመጡና ተገቢው እድሳት የሚደረግለት መሰብሰቢያ ቦታ ይሖዋንና ሕዝቦቹን እንደሚወክል መዘንጋት አይገባም።
5 ዕቃዎች እንዳይሰበሩ ወይም እንዳይበላሹ ሁሉም ጥንቃቄ የሚያደርግ ከሆነ ቶሎ ቶሎ መታደስ አያስፈልገውም። ከቁመት በላይ በሆኑ ነገሮች ላይ ለመድረስ ከፕላስቲክ በተሠሩ ወይም በቀላሉ ሊሰበሩ በሚችሉ ወንበሮች ላይ መቆም የተለመደ ነው። አብዛኞቹ ወንበሮች ለዚህ ዓላማ ስላልተሠሩ በተደጋጋሚ በዚህ መንገድ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ከዋሉ ይጎዳሉ። ወንበር ሥር ማስቲካ መለጠፍ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። በዕቃዎች ወይም በወለሉ ላይ ማስቲካ መለጠፍ፣ ወረቀት ወይም ሌሎች ነገሮችን በግድ የለሽነት መጣል፣ በቆሻሻ እጅ ግድግዳ መንካት ወይም እግር ሳይጠርጉ ወደ አዳራሽ መግባት በሌሎች ላይ ሥራ መጨመር እንደሆነ መገንዘብ ያሻል። እያንዳንዱ ሰው ጥንቃቄ ቢያደርግ ጥሩ ነው።
6 ትንንሽ ልጆች በመንግሥት አዳራሽ መገኘታቸው በጣም የሚያስደስት ነው። ከይሖዋ ቃል የሚሰጠውን ትምህርት ለማግኘት እነርሱም ከወላጆቻቸው ጋር መገኘት ይገባቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው። ልጆች ወንበሮችን ሲፍቁ ወይም በላዩ ላይ ሲጽፉ ዝም ብሎ ማየት አይገባም። ከስብሰባ በፊትና በኋላ እየተሯሯጡ መጫወት ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ በሌሎች ሰዎችና በዕቃዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ሥርዓት የሌላቸው ‘ያልተቀጡ’ ልጆች ሌሎችን ያሳፍራሉ። (ምሳሌ 29:15) ሽማግሌዎች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ቀርበው ካነጋገሩህ አዳራሹ ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ምቹ እንዲሆን ለማድረግ አስበው እንደሆነ በመገንዘብ እሺ ባይና አመስጋኝ ሁን። ሁላችንም እነዚህን ማሳሰቢያዎች በመታዘዝ የመንግሥት አዳራሻችንን ቸል እንዳላልን በማሳየት ድርሻችንን መወጣት እንችላለን።—ነህ. 10:39