የአስተዳደር አካል ደብዳቤ
ምንኛ የታደልን ነን! የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እውነተኛና ሕያው የሆነውን የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ይሖዋን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ስሙን የመሸከምና እሱን የማገልገል መብትም አግኝተናል። ከዚህ የሚበልጥ ምን በረከት ሊገኝ ይችላል!—ኢሳ. 43:12፤ ዕብ. 8:11
የመዳን ተስፋ አለን እንዲሁም ሌሎች እንደ እኛ ይሖዋን እንዲያመልኩና ተስፋችንን እንዲጋሩ ለመርዳት የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቶናል። (ማቴ. 24:14፤ ሮሜ 10:13, 14፤ 1 ተሰ. 5:8) እንዲሁም እርስ በርስ የምንፋቀርና የምንረዳዳ ለአንድ አምልኮ የተሰለፍን ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አካል የመሆን አስደሳች መብትም አግኝተናል። ይህ ሁሉ ምንኛ አርኪ ነው!
መጽሐፍ ቅዱስ “በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ [“ይሖዋን አገልግሉት፣” NW ]፣ . . . ወደ ደጆቹ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፣ ስሙንም ባርኩ፤ እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና” የሚል ግብዣ ማቅረቡ የተገባ ነው። (መዝ. 100:2-5) ይሖዋን በደስታ ማገልገል ከእርሱ ጋር በግል የጠበቀ ወዳጅነት ከመመሥረት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። እርሱ ይህን ዝምድና እንድንመሠርት መንገዱን የሚያመቻች ሲሆን እኛ ደግሞ ወዳጅነቱን የማጎልበት መብት አለን። እንደዚህ ያለ ወዳጅነት ስንመሠርት ይሖዋ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ለመርዳትና እኛን ለማበርታት ዝግጁ እንደሆነ እናውቃለን። በዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ስንኖር የሚገጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች እንድንቋቋም የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ብርታትና መመሪያ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። የተለያዩ ችግሮችን መጋፈጥ ቢኖርብንም በአገልግሎታችን ደስተኞች ነን። እንዲሁም ቃሉ ‘እሱ ስለ እኛ እንደሚያስብ’ ስለሚያስታውሰን ይሖዋን በየዕለቱ እናመሰግነዋለን።—1 ጴጥ. 5:7
ባለፈው ዓመት ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኮናል። “የአምላክ ቃል አድራጊዎች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከእኛ ጋር የተካከለ የክብር እምነት ካላቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር በመሰብሰባችን፣ በኅብረት በመዘመራችንና ይሖዋ ካዘጋጀው መንፈሳዊ ገበታ በመመገባችን ተደስተናል። በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናታችን ላይ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ በአንድነት ማጥናታችን እምነታችንን የምናጠነክርበት አጋጣሚ ፈጥሮልናል። ከዚህም በላይ የኢሳይያስ ትንቢት —ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን! የተባለውን አዲስ ጽሑፍ የመጀመሪያ ጥራዝ ማግኘታችን ምንኛ አስደሳች ነበር! ‘ጽዋችን ሞልቶ ተትረፍርፏል።’—መዝ. 23:5
በመንፈሳዊ ወንድማማችና እህትማማች የሆንን በሚልዮን የምንቆጠር ሰዎች ይሖዋን በማገልገል አንድ ግንባር መፍጠራችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! በመስክ አገልግሎት ረገድ አዳዲስ ከፍተኛ ቁጥሮች መገኘታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶችን ማንበቡ ምንኛ አበረታች ነው! የዓለም ሁኔታ ምንም ዓይነት ይሁን በጌታችን ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መገኘታቸው አስደስቶናል። ዓለም አቀፉን መስክ ስንመለከተው ‘መከሩ ብዙ’ እንደሆነ በግልጽ እናስተውላለን። (ሉቃስ 10:2) ባለፈው ዓመት በእያንዳንዱ ሳምንት በአማካይ 5, 555 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ራሳቸውን ወስነው ለመጠመቅ በቅተዋል። መከሩ በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ላይ ከሌሎች ይልቅ ብዙ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ እያከናወነ ባለው ሥራ ደስ ይለናል። የአገልጋዮቹን የተባበረ ጥረት እየባረከ እንዳለ በግልጽ እየተመለከትን ነው።
በእጅጉ እንድንደሰት ያደረገን ሌላው ነገር የአዳዲስ መንግሥት አዳራሾች ግንባታ ነው! በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይህን ሥራ በሙሉ ልብ ሲደግፉ ማየታችን በጣም አስደስቶናል። አስፈላጊው ስልጠና በተሰጣቸው የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች እርዳታ እስከ አሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል። እነዚህ ወንድሞች በአገራቸው ውስጥ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይሠራሉ። ከዚህ በኋላም በሺህ የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ስለሚያስፈልግ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ በዚህ መስክ የሚሰማሩ ተጨማሪ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። የምትኖረው ከእነዚህ አገሮች በአንዱ ውስጥ ከሆነ ራስህን ለሥራው ማቅረብ ትችላለህ? ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለአምልኮ የሚሰበሰቡበት የራሳቸው የመንግሥት አዳራሽ ማግኘታቸው ምንኛ ያስደስታቸዋል! ሥራው እንዲሠራ የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርግላቸው ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ምንኛ አመስጋኞች ናቸው!
በፍርድ ቤት ስላገኘናቸው ድሎች ስንሰማ እንደሰታለን። ይሁን እንጂ በብዙ ቦታዎች የይሖዋን አምልኮ ለማዳፈን የሚጥሩ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አሉ። ከእነዚህ ችግሮች ጋር በምናደርገው ትግል ተቃዋሚዎች የቱንም ያህል ቢበዙ ወይም አገልጋዮቹ የቱንም ያህል በቀላሉ ማጥቃት የሚቻል መስሎ ቢታይ ይሖዋ ሕዝቦቹን ከመርዳት የሚያግደው አንዳች ነገር እንደሌለ እርግጠኞች ነን። (2 ዜና 14:11) ለእውነተኛው አምልኮ ጸንታችሁ የቆማችሁትን ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ከልብ እናመሰግናችኋለን።
ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችሁን በምትወጡበት ጊዜ እምነታችሁን ማጠንከራችሁንና መመሪያ እንዲሰጣችሁ በይሖዋ ላይ መደገፋችሁን ቀጥሉ። (ምሳሌ 3:5, 6) ጠላት ምንም ያድርግ ምን ልባችን የሚዝልበት ምክንያት የለም። ኤልሳዕ በጭንቀት ተውጦ ለነበረው አገልጋዩ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” በማለት የሰጠውን ማበረታቻ አስታውሱ። (2 ነገ. 6:15-17) የይሖዋ ሰማያዊ ሠራዊት በኤልሳዕ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም የንጹሑን አምልኮ ፍላጎቶች ለማስከበር በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል። ከይሖዋ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ምንም ነገር ስለሌለ የወደፊቱን ጊዜ ያለ ስጋት እንጠባበቃለን። ብሔራት ይሖዋን ቅንጣት ታክል ሊገዳደሩት አይችሉም። ይሖዋ ልጁን ሙሉ ሥልጣን ሰጥቶ አንግሦታል። “በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።”—መዝ. 2:1-6, 12
ውድ ወንድሞችና እህቶች ስለ ሁላችሁ ዘወትር ከልብ እንደምናስብ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። እያንዳንዳችሁ “ምሉዓን ሆናችሁና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯችሁ እንድትቆሙ” ከልብ እንጸልያለን።—ቆላ. 4:12 NW
ወንድሞቻችሁ፣
የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል