የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 9/01 ገጽ 4
  • ለስብከቱ ሥራ እንቅፋት ይሆናልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለስብከቱ ሥራ እንቅፋት ይሆናልን?
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ‘ምን ጊዜም አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’
    እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • ‘ከሁሉ አስቀድመህ መንግሥቱን ፈልግ’
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • ከሥራህ እርካታን ማግኘት ትችላለህ
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
km 9/01 ገጽ 4

ለስብከቱ ሥራ እንቅፋት ይሆናልን?

1 የአብዛኞቹ ሰዎች ሕይወት በሥራ የተጠመደ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችም በጣም ሥራ ከሚበዛባቸው ሰዎች መካከል ናቸው። የአምላክን ቃል ያጠናሉ፣ በጉባኤ ስብሰባዎቸ ላይ ይገኛሉ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ይካፈላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሰብዓዊ ሥራችን፣ የቤት ውስጥ ወይም የትምህርት ቤት ሥራችን እና ያሉብን ሌሎች ብዙ ኃላፊነቶች ጊዜያችንን ይሻሙብናል። በተለይ ለቤተሰብ ራሶች ሁኔታው ተፈታታኝ ነው።

2 በተለያዩ ቦታዎች ባለው አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት ብዙ የቤተሰብ ራሶች መተዳደሪያ ለማግኘት ለረዥም ሰዓታት ጠንክረው መሥራት ይኖ​ርባቸው ይሆናል። ፋታ የማይሰጠው ሰብዓዊ ሥራቸው አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ስለሚያሟጥጠው ለስብከቱ ሥራ የሚኖራቸው ጊዜና ጉልበት ትንሽ ይሆናል። አንዳንዶች የቤተሰባቸውን ሰብዓዊ ፍላጎት የማሟላት ግዴታ ስላለባቸው በስብከቱ ሥራ ሊኖራቸው የሚችለው ተሳትፎ ውስን እንደሆነ ይሰማቸዋል። (1 ጢ⁠ሞ. 5:8) ዛሬ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ነገሮች ከማሟላት ጋር የተያያዙ ብዙ ጭንቀቶች መኖራቸው አይካድም። ሆኖም የአንድ ሰው ሰብዓዊ ሥራ ምሥራቹን እንዳይሰብክ እንቅፋት ሊሆንበት አይገባም። (ማር. 13:10) እንግዲያው ያለንበትን ሁኔታ መመርመራችን ተገቢ ነው።

3 የዓለም ሁኔታ ሁልጊዜ ተለዋዋጭ በመሆኑ አንድ የቤተሰብ ራስ ለክፉ ቀን የሚሆን መጠባበቂያ ገንዘብ ለማጠራቀም ረዥም ሰዓታት መሥራት እንደሚገባው ይሰማው ይሆናል። (1 ቆ⁠ሮ. 7:31) ለረዥም ሰዓታት ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የሚያስገኝ ወይም ሰፊ የመዝናኛ አጋጣሚዎች የሚከፍት ቢመስልም ይህንን የምናደርገው ለመንፈሳዊ ነገሮች ወይም አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምናውለውን ጊዜ መሥዋዕት አድርገን ከሆነ ይህ ቤተሰቡን ደስተኛና ባለው ረክቶ የሚኖር ሊያደርገው ይችላልን? መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር ለማስወገድ እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ ‘በሰማይ መዝገብ እንድንሰበስብ’ እና “በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ” እንድንሆን የሰጠንን ምክር መከተሉ የጥበብ መንገድ ነው።​—⁠ማቴ. 6:19-21፤ ሉቃስ 12:15-21

4 መንግስቱን አስቀድሙ:- ኢየሱስ መንፈሳዊ ነገሮችን ከማንኛውም ነገር በፊት እንዲያስቀድሙ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል። “እንግዲህ:- ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ” በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል። እንዲህ ያለው ለም​ንድን ነው? “ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና” ሲል አብራርቷል። በዚህ አባባል በእርግጥ የምናምን ከሆነ ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረውን ከማድረግ የሚያግደን ነገር አይኖርም። “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ [የሚያስፈልጋችሁ ቁሳዊ ነገር] ይጨመርላችኋል።” አምላክ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንድናገኝ ያደርጋል! (ማቴ. 6:​31-33) ያለንበት ወቅት ስለኑሮ ከልክ በላይ በመጨነቅ ወይም በቅርቡ በሚጠፋ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ተደላድለን ስለመኖር በማሰብ ትኩረታችን በሌላ ነገር እንዲወሰድ የምንፈቅድበት ጊዜ አይደለም።​—⁠1 ጴ⁠ጥ. 5:​7፤ 1 ዮሐ. 2:​15-17

5 አንድ ሰው ሰብዓዊ ሥራ የሚሠራበት ዋነኛ ዓላማ ቁሳዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ነው። ነገር ግን የሚያስፈልገን ምን ያህል ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” ሲል ጽፏል። ከዚያ የበለጠ ነገር ለማግኘት እየጣርን ነውን? ከሆነ ጳውሎስ “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” ሲል አስቀድሞ ያስጠነቀቀው ነገር እየደረሰብን ሊሆን ይችላል። (1 ጢ⁠ሞ. 6:8, 9፤ ማቴ. 6:24፤ ሉቃስ 14:33) ከልክ ያለፈ ምኞት እንቅፋት ሆኖብን እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

6 በሰብዓዊ ሥራችን ምክንያት በመስክ አገልግሎት ያለን ተሳትፎ ዝቅተኛ ከሆነ ወይም ለምሥራቹ ስንል መሥዋዕትነት የመክፈሉ አስፈላጊነት የማይታየን ከሆነ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገናል ማለት ነው። (ዕብ. 13:15, 16) ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አኗኗር ለስብከቱ ሥራ እንቅፋት የሆነብንን ነገር ለማስወገድ ይረዳናል። በጊዜና በጉልበት አጠቃቀማችን ረገድ የመንግስቱ ፍላጎቶች ምንጊዜም ቢሆን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል።

7 ለከንቱ ያልሆነ ድካም:- የጳውሎስ ቃላት ‘ድካማችን በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቀን የምንደላደል፣ የማንነቃነቅ፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛልን እንድንሆን’ ያበረታቱናል። (1 ቆ⁠ሮ. 15:​58) ከሁሉ የላቀው ‘የጌታ ሥራ’ የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:​19, 20) የሚቻለንን ያህል ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ በየሳምንቱ ለመስክ አገልግሎት የተወሰነ ሰዓት መመደብና ያንን ሰዓት ለሌላ ለምንም ዓይነት ሥራ ላለማዋል መጣር አለብን። (ኤፌ. 5:15-17) እንዲህ ካደረግን ሰብዓዊ ሥራም ሆነ ሌላ ማንኛውም ነገር ለአገልግሎታችን እንቅፋት አይሆንብንም።

8 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል ራሳችንን ስናቀርብ ከመስጠት የሚገኘው ከሁሉ የላቀ ደስታ ይኖረናል። (ሥራ 20:35) ‘እግዚአብሔር ያደረግነውን ሥራ ለስሙም ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም።’ የመንግሥቱን ስብከት ሥራ እያከናወንን የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት ልንጠባበቅ እንችላለን።​—⁠ዕብ. 6:10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ